የሲቪል ማህበራት ተቋማት በቀጣይ በኢትዮጵያ በሚኖረው ምርጫ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

የሲቪል ማህበራት ተቋማት በቀጣይ በኢትዮጵያ በሚኖረው ምርጫ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ የፀደቀውን የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ውይይት እየተደረገ ሲሆን፤ በዚሁ መድረክ የሲቪል ማህበራት ተቋማቱ በቀጣይ በኢትዮጵያ በሚኖረው ምርጫ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ብሌን አስራት ቦርዱ ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፤በአገሪቱ በተካሄዱት ምርጫዎች የሲቪል ማህህበራት ተቋማት ሚና አናሳ እንደነበር አስታውሰዋል።

ባለፉት ዓመታት የሲቪል ማህበራት በአገሪቱ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን እንዳይወጡ በማህበራቱ ላይ የነበሩት አሳራሪ አሰራሮች የማህበራቱን እንቅስቃሴ ውስን እንዲሆን አድርጎት ቆይቷል ብለዋል።

የሲቪል ማህበራቱ በቀጣይ በሚኖረው አገራዊ ምርጫ ህብረተሰቡን በምርጫ ስነ ምግባርና ደንቦች ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖረው የተለያዩ ስልጠናዎች በመስጠት መስራት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

የሲቪል ማህበራቱ በቀጣዩ ምርጫ ሂደትም ገለልተኛ ታዛቢዎችን በማሰማራት በሂደቱም ከምርጫ በኋላም በሚኖረው የምርጫው ተአማኒነት ሚናቸውን እንዲወጡ ዋና ዳይሬክተሯ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አባል ወይዘሪት ብዙወርቅ ከተተ በበኩላቸው፤ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጁ ምንም እንኳ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀ ቢሆንም፤መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በቦርዱ ለሚወጡ መመሪያዎች ግብአት የሚገኝበት ይሆናል ብለዋል።