ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ሌሎች ዜጎች የተፈጸመውን ጥቃትና የንብረት ዝርፊያ አወገዘ

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ የሌሎች የአፍሪካ አገራት ዜጎች ኢላማ ባደረገ መልኩ የተፈጸመውን ጥቃትና የንብረት ዝርፊያ በፅኑ እንደሚያወግዝ አስታወቀ፡፡

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራሞፎሳ ድርጊቱን በማውገዝ በጉዳዩ ላይ የተሳተፉ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ እንደሚያቀርቡ የገቡት ቃል አበረታች መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በገቡት ቃል መሰረትም በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን ለህግ እንደሚያቀርቡ እንደሚያምንና በየደረጃው የሚገኙ የደቡብ አፍሪካ ባለስልጣናት ጠንካራ ክትትል በማድረግ በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን በቁጥጥር ስር እንዲያውሉና ለህግ እንዲያቀርቡ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ዜጎቻችን ደህንነት እንዲጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉ ሚኒስቴር ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲም ከሚመለከታቸው የአገሪቱ ባለስልጣናት እና ከኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ጋር ሁኔታውን ለማረጋጋት በቅርበትና በትብብር እየሰራ መሆኑንና በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከሚኒስቴሩ ቃልአቀባይ ያገኘኘው መረጃ ያመለክታል፡፡