ክረምቱን ተከትሎ የወባ ወረርሽኝ እንዳይከሰት ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጤና ሚኒስቴር አሳሰበ

የክረምት ዝናብን ተከትሎ የወባ ወረርሽኝ እንዳይከሰት ህብረተሰቡ ከወዲሁ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ  ማድረግ እንደሚገባው የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።

የጤና ሚኒስቴር ለዋልታ በላከው መግለጫ በወባ በሽታ መከላከል፣ መቆጣጠርና ማስወገድ ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን አጠናክሮ በመቀጠል የወባ ወረርሽኝ እንዳይከሰትና በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደርግ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

የክረምት ዝናብን ተከትሎ ከመስከረም እስከ ታህሳስ ወር ያለው ጊዜ በኢትዮጵያ ዋነኛ የወባ መተላለፊያ ወቅት መሆኑን በመጥቀስ፤  የወባ በሽታ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ዕድሜም ሆነ ፆታ ሳይለይ የሚያጠቃ የጤና ጠንቅ በመሆኑ በሽታው እንዳይከሰት ህብረተሰቡ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል ተብሏል።

በወባ ትንኝ አማካይነት ሊከሰት የሚችል የህመምና የሞት መጠንም በመቀነስ በሽታውን ለመቆጣጠርና ለማስወገድ በአገሪቷ የተለያዩ ስልቶች ተነድፈው በመተግበር ላይ መሆናቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ከኢትዮጵያ ቆዳ ስፋት ውስጥ 75 በመቶ የሚሆነው ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ መሆኑንና  60 በመቶ የሚሆነው ህዝብም በነዚህ አካባቢዎች የሚኖር መሆኑ ለበሽታው ተጋላጭ እንደሚያደርገው የጠቆመው የሚኒስቴሩ መግለጫ፤ የክረምቱን መውጣት ተከትሎ በሚከሰተው የዝናብ መቆራረጥ ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታዎችን ስለሚፈጥር ዜጎች ተገቢው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አበ2018 ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ከ2010 እሰከ 2017 የወባ ህሙማን ቁጥር በ50%፣ ሞት ደግሞ በ60% ቀንሷል እድቀነሰ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፤ በሀገር ደረጃ የተደረገው ጥናት (ከ1997 ዓ.ም እሰከ 2008 ዓ.ም) በወባ በሽታ የሚከሰተው ሞት በ80% መቀነሱን ተመልክቷል፡፡

ባለፉት14 ዓመታት ደግሞ  በሀገር አቀፍ ደረጃ ምንም ዓይነት የወባ ወረርሽኝ አለመከሰቱን የሚኒስቴር መስሪያቤቱ መግለጫ ያመለከተ ሲሆን፤ በ2011 በጀት ዓመትም ማጠቃለያ ላይ በተከናወኑ ስራዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ሚሊዮን በታች የወባ ህሙማን ቁጥር ሪፖርት መኖሩን አስታውሷል።