አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ በ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ስራ ላይ በሚውልበት አግባብ ላይ ገለጻ ተደረገ

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች ጋር ባካሄደው የጋራ መድረክ አዲሱ የስርዓተ ትምህርት ፍኖተ ካርታ በ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ስራ ላይ በሚውልበት አግባብ ላይ ገለጻ ተደርጓል፡፡

የዓለም ነባራዊ የቴክኖሎጂ ደረጃ ጋር የሚጓዝ ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደርጉት ድጋፍ የሚጠበቅ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማሪያም ገለጹ፡፡

በትምህርቱ ዘርፍ የሚስተዋለውን ክፍተት ለመድፈን ሲባል መንግስት ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ እያደረገ ያለው ማሻሻያ እና ክለሳ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደሚዘልቅም በፍኖተ ካርታው ተዳሷል፡፡

ከግል የትምህርት ተቋማት ጋር በተደረገው የምክክር መድረግ እንደተብራራዉም ዓለም ባሁኑ ወቅት ወደ ተሸጋገረችበት የአራተኛው የቴክኖሎጂ ዘመን የሚጠይቀውን ብቃትና አቅም ለማዳበር ተማሪዎች ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር እንዲራመዱ ይፈለጋል፡፡

ሃገሪቱ ባለፉት 20 ዓመታት በትምህርቱ ዘርፍ ተደራሽነት ላይ የሰራቻቸው ጉልህ ስኬቶች ተጠቃሽ ቢሆኑም በጉዞው ላይ የገጠሙ የጥራት ጉድለቶች በትኩረት ሊሰራባቸው የሚገባ ስለመሆኑ ነው የተብራራው፡፡

የተማሪዎች የሳይንስ ትምህርት ውጤት እጅጉን አሽቆልቁሎ ተስተውሏል፡፡ ብቃት ያላቸው መምህራን የማፍራት ችግር ደግሞ ለዚህ ጉልህ ሚናን ተጫውቷል ነው የተባለው፡፡ ለአብነትም ከ2006-2009 በተደረገው ጥናት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተወዳደሩት መምሀራን የተሰጠዉን ፈተና ከ50 ከመቶ በላይ ማስመዝገብ የቻሉት የተፈታኞቹ 11 በመቶ ብቻ መሆኑም በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡

ለዚሁ ክፍተት እንደማቃለያነት የተለያዩ መፍትሄዎች ተወስደዋል፡፡ ለአብነትም የተማሪዎች የተግባቦት አቅም፣ የማገናዘብ እና የግብረገብነት አቅማቸውን በሚያበለጽግ መልኩ የተቃኙ አዳዲስ ኮርሶች ተቀርጸው ከአዲሱ የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁሉም የከፍተኛ ት/ት ተቋማት መሰጠት እንደሚጀመርም በመድረኩ ይፋ ሆኗል፡፡

እስካሁን በተደረገውና በመድረኩም የቀረበው ጥናት እንደሚያመለክተዉ የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከግሉ ዘርፍ ጋር ሲነጻጸር የተሻለ አቅም ያላቸው ተማሪዎችን እንደሚያበቁ ነው የተገለጸው፡፡ ይሁንና የግሉ ዘርፍ በተደራሽነትም ሆነ በጥራቱ ማሻሻያ ከፍተኛ ስራ የሚጠበቅበት መሆኑን በመግለጽ ጥናቱ የመፍትሄ ሃሳቦችን በማመላከት በተሳታፊዎች ተመክሮበታል፡፡

ዋልታ ያነጋገራቸው የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች በበኩላቸው በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ላይ በየደረጃው ሲመክሩበት መቆየታቸውን ገልጸው፤ ዘርፉ የታለመለትን ጥራት ያለው የሰው ኃይል ለኢንዱስትሪው እንዲያቀርብ ከወዲሁ ትስስሮች እንዲፈጠሩ ጠይቀዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ለግሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘርፍ እገዛ እንደሚያደርግ ነው ያስታወቀው፡፡