ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ተወያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ዛሬ ጠዋት በቢሯቸው ነው የተወያዩት፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በተደረገው ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከለውጡ ወዲህ መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ያለውን አቋምና ያከናወናቸውን ተግባራት አውስተዋል፡፡

ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስና ሌሎችም ሊቃነ ጳጳሳት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ለሀገርና ለቤተክርስቲያን የተከናወኑ በጎ ተግባራትን በመዘርዘር ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በለውጡ ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች በውይይቱ ላይ የተነሡ ሲሆን፣ በአንዳንድ አካላት እየተፈጸሙ ያሉ ጥፋቶችን በማንሣት ጳጳሳቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም የእርሳቸውም ሆነ የመንግሥታቸው ፍላጎት የተጠናከረች፣ ለሀገር ግንባታ የሚቻላትን ሁሉ የምታደርግና አንድነቷ የተጠበቀ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ማየት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የእምነት ተቋማት መጠናከርና አንድ መሆን ጥቅሙ ለእምነት ተቋማቱ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ጭምር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የቀረቡት ችግሮች በለውጥ ውስጥ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱ ሲሆን፣ ዓይነታቸው ቢለያይም የተለያዩ የእምነት ተቋማት በለውጡ ሂደት ፈተና አጋጥመዋቸዋል፣ በመሆኑም ዕንቅፋት የሚፈጥሩትን አካላት መታገል ያለብን በጋራ ነው ብለዋል፡፡

የቀረቡትን ችግሮች በዝርዝር በማጥናትና በየደረጃው ካሉ አመራሮች ጋር በመነጋገር በጋራ እንደሚፈቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በሀገር ላይ የሚደርሱ ጥፋቶች በሁሉም ላይ የሚደርሱ በመሆናቸው መንግሥትና የእምነት ተቋማት በጋራ በመሥራት መፍታት እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም የተፈጠሩትን ችግሮች የጋራ በማድረግ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነትና ክብር በጠበቀ መልኩ በጋራ ለመፍታት ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ (ምንጭ፡-የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት)