የብሄራዊ ኩራት ቀን በመስቀል አደባባይ በድምቀት ተከበረ

የብሄራዊ ኩራት ቀን "አዲስ አበባ ቤቴ ፤ ኢትዮጵያዊነት ኩራቴ!" በሚል መሪ ቃል በዛሬው እለት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በድምቀት ተከበረ፡፡

በስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ  ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት በህዝቦቿ አንድነት መቆየቷን ጠቅሰው ፤ይህ አንድነት የሀገሪቱ ብሄራዊ ኩራት ነው ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያ፣ የሁሉም ባህል መገለጫ  ዋና ከተማ እንደመሆኗ የዛሬውን ብሄራዊ የኩራት ቀን በዚህ መልኩ ነዋሪዎቿ  በድምቀት በማክበራቸው ክብር ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡

የብሄራዊ የኩራት ቀን ብሄራዊ እሴቶችን  አጉልቶ በሚያሳይና ለነገ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንዲተባበር መነቃቃትን መፍጠር በሚያስችል መልኩ በከተማችን በተለያዩ መርሃ-ግብሮች ይከበራል፡፡

ከ250 ሺህ በላይ ሰው ተሳታፊ የሆነበት ህዝባዊ ትእይንት በመስቀል አደባባይ ከጠዋቱ 12፡30 ጀምሮ ተካሂዷል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት የወታደራዊ እና የአየር ሃይል ትርዒት ያቀረበ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪዎች እና የበረራ ሰራተኞች ጨምሮ ብሄራዊ ኩራት የሆኑ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ተቋማት የሚወከሉበት ትርዒት ቀርቧል፡፡

በበዓሉ ላይ ከፍተኛ የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡