በሀገሪቱ ከ38 ዞንና 42 ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎች  ወደቀያቸው ተመለሱ

ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ  ከማድረግ ጎን ለጎን በ38 ዞንና 42 ወረዳዎች ጥናት በማድረግ መልሶ ማቋቋም መቻሉ  ተገልጿል።

የሰላም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሄርሜላ ሰለሞን  እንዳሉት ተቋማቸው ሰላም፣ መተሳሰብና ፍቅር የሞላባት ኢትዮጵያን ለመገንባት በሰላምና ብሄራዊ መግባባት፣በህግ ማስከበር፣ በፌደራሊዝም ና ተመጣጣኝ ልማት የአቅም ግንባታ በማዘመን ዘርፎች ሰርቷል፡፡

ሰላም ከውይይት ይመነጫል ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ይህን የሚያሳኩ የሴቶች ፣የሀገር ሽማግሌዎች ፣የወጣቶች ፣የሚድያና የኪነጥበባት ባለሙያ ውይይት መካሄዱን አስረድተዋል፡፡

በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን የመፍጠርና ግጭቶችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ያለሙ በሱማሌና ኦሮሚያ፣ በአፋርና ሶማሌ፣በደቡብና ኦሮሚያ  መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ እንደተካሄደ መናገራቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በ38 ዞንና 42 ወረዳዎች ጥናት በማድረግ መልሶ የማቋቋም ስራዎች በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣በኦሮሚያ፣በአማራ፣በሶማሌ፣ በትግራይና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደር መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

ግጭቶችን  በማነሳሳት  የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለህግ ማቅረብ፣ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ክልሎችን ያሳተፉ የህዝብ ውይይቶች ጥሩ ጅምር እንደሆነም ነው የተናገሩት።

“እኔ ሰላም ስሆን ሌላውን ሰላም ማድረግ እችላለሁ” የሚለው  አስተሳሰብ   አለመዳበሩ የህብረተሰቡን የህግ የበላይነት ይከበር ጥያቄን ለማርካት  እንቅፋት መሆኑንም  ዳይሬክተሯ  ተናግረዋል።

በያዝነው በጀት  አመትም  ዘላቂ ሰላምን  እውን ለማድረግ የውይይትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ለህግ የበላይነት መከበር  በአጽንኦት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡