ኮሚሽኑ በበዓል ወቅት ህብረተሰቡ ከእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች እንዲጠነቀቅ አሳሰበ

በዘመን መለወጫ በዓል ህብረተሰቡ ከእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች እንዲጠነቀቅ የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን  አሳስቧል፡፡

በበዓሉ ወቅት ከእሳ ፍጆታ መጨመርና ሰፊ የመዝናናት ስሜት ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለውን የእሳት ቃጠሎና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎችን ትኩረት በመስጠት መከላከል እንደሚቻልም ነው ኮሚሽኑ የገለፀው፡፡

በመሆኑም በመኖሪያ ቤት እንደ ጧፍ፣ የጋዝና ኤሌክትሪክ ምድጃዎችን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብሏል፡፡

በተለይም በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰሩ መሳሪያዎችን በአንድ ሶኬት ደራርቦ ከመጠቀም መቆጠብ፣ ከኤሌክትሪክ አጠቃቀም ችግር እሳት ቢነሳ በውሃ ለማጥፋት መሞከር አይገባም ነው ያለው፡፡

ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ካምፕ ፋየር የእሳት አደጋ በማያስከትል መልኩ በጥንቃቄ መዘጋጀት እንዳለበትና በተለይ አስጊ በሆኑት እንደ ነዳጅ ማደያ ባሉ አካባዎች ግን ፈፅሞ መዘጋጀት እንደሌለበት አሳስቧል፡፡

ጠጥቶ ከማሽከርከር በመቆጠብ ሊደርስ የሚችለውን የህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት አስቀድሞ መገንዘብና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ የእሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ቢከሰቱ  በሚከተሉት የስልክ ቁጥሮች መጠቀም እንደሚቻል አስታውቋል ፡፡

ለዋናው ማዕከል 0111555300 ወይም 0111568601 ወይም በነፃ የሥልክ ጥሪ 939 መጠቀም እንደሚቻል ነው የገለፀው፡፡

ኮሚሽኑ በዘጸኙም ቅርንጫፍ ፅህፈትቤቶቹ የ24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱንም ለዋልታ ቴሌቭዥን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡