ማህበራቱ ከቤተክርስቲያኗ ጋር በተያያዘ መስከረም 4፤2012 ዓ.ም የሚካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ አስመለክተው መግለጫ ሰጡ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ማህበራት መስከረም 4፤2012 ዓ.ም የሚካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ አስመለክተው መግለጫ ሰጡ፡፡

መግለጫውን የሰጡት የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴዎች በቤተክርስቲያን እየደረሰ ያለውን የመቃጠል፣ የካህናት መገደልና ሌሎች በቤተክርስቲያንቱ ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለማውገዝ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ሰልፉን በማስመልከት ዝርዝር መግለጫዎችን በመስከረም 2፤2012 ዓ.ም እንደሚሰጥ የገለጸው ኮሚቴ፣ የነበራቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ከመንግስት አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ እንደሆነና በውይይቱ አጥጋቢ መልስ ካገኙ ሰልፉ ሊቀር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ማህበራቱ የሰላማዊ ሰልፍ መካሄድ አለመካሄዱንም በቀጣይ መስከረም 2 በሚኖረው ድጋሚ መግለጫ እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ሰልፉ ከኦሮሚያ ክልል ቤተክህነት ምስረታ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ በመጠቆም ከኦሮሚያ ቤተ ክህነት ምስረታ ጋር በተያያዘ በጉዳዩ ዙሪያ በቅርቡ ሲኖዶሱ የሰጠው መግለጫ በቂ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ሰልፉን ለማዘጋጀት ከባለፈው አንድ ወር ጀምሮ እየተንቀሳቀሱ እንደቆዩም የጠቆሙ ሲሆን፤ የሰልፉ አላማም በሰላማዊ መንገድ በቤተክርስቲያኒቷ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለማውገዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የታቀደው ሰልፍ ሰልፍ  በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደሚሆንና  ህዝበ ክርስቲያኑ ከቤተክርስቲያንቷ ጎን እንዲቆሙም ጠይቀዋል፡፡