ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የአልባሳት ስጦታና የምሳ ግብዣ አደረጉ

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አዲሱን ዓመት 2012 ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ የህፃናት ማሳደጊያዎች ለተውጣጡ ታዳጊዎች የአልባሳት ስጦታ እና የምሳ ግብዣ አደረጉ፡፡

ቀዳማዊት እመቤቷ ከ18 የህፃናት ማሳደጊያዎች ለመጡ 650 ለሚሆኑ ታዳጊዎች የአልባሳት ድጋፍ በማድረግ ታዳጊዎቹ መተሳሰብ፣ መረዳዳት እና አብሮነትን እንዲላመዱ ለማስቻል በቤተ-መንግስት አዲስ ዓመት ዋዜማን በሚኒሊክ አዳራሽ አክብረዋል፡፡

ታዳጊዎቹም በቤተመንግስት ቅጥር ግቢ ውስጥ እየተሰራ ያለውን የእድሳት ስራና ታሪካዊ አሻራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በተዘጋጀው ክብረ በዓል ላይ የቁርስ እና የምሳ ግብዣ ለህፃናቱ የተደረገ ሲሆን ህፃናቱም የተለያዩ ትዕይንቶችን አቅርበዋል።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ከዚህ በፊት ከ400 በላይ ለሚሆኑ ህፃናት በተመሳይ ድጋፍ አድርገው በዓሉን በጋራ አክብረዋል፡፡