ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ ከፈረንሳዩ የባህል ሚንስትር ፍራንክ ራይስተር ጋር ተወያዩ

ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ ከፈረንሳዩ የባህል ሚንስትር ፍራንክ ራይስተር ተወያዩ

ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ በፈረንሳይ መንግስት ድጋፍ እየተካሄዱ ያሉት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና የኢዩቤልዩ ቤተመንግስት እድሳት ዙሪያ ከፈረንሳዩ የባህል ሚንስትር ፍራንክ ራይስተር ጋር ተገናኝተው ተወያዩ::

የኢትዮጵያና የፈረንሳይን ጠንካራ ግንኙነትና የፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ጥልቅ የትብብር ፍቃደኝነት ያነሱት ጠ/ሚር ዐቢይ እድሳቱን ማፋጠን እንዲቻል አበረታትተዋል::

ራይስተር በበኩላቸው የዛሬው ጉብኝታቸው ፕሬዝዳንት ማክሮን ለሁለቱም ሀገራት የሚበጅ የቅርስ ጥበቃ ላይ ለመተባበር ያላቸውን ፍቃደኝነት ማሳያ ነው በማለት የቴክኒክና የልምድ ልውውጥም ለማድረግ ይረዳልም ብለዋል::

የኢዩቤልዩ ቤተመንግስትን እድሳት በተመለከተ አስፈላጊው ጥናት እየተጠናቀቀ ሲሆን፤ እድሳቱ በጥቂት ወራት ውስጥ ተጀምሮ በፍጥነት ለቱሪስት ጉብኝት የሚከፈት ይሆናል ተብሏል::

የቱሪዝም ዘርፍን ማጎልበት የኢትዮጵያ መንግሥት ለሥራ ፈጠራና ኢንቨስትመንት ለመሳብ ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ዋነኛው መሆኑንና ለዚህም የቅርስ ጥበቃና ክብካቤ ቅድሚያ የሚሰጠው የዘርፉ አካል መደረጉን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።