አረጋውያንን መንከባከብ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ

አረጋውያንን መንከባከብና መርዳት በችሮታ የሚደረግ ሳይሆን የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት መሆን እንደሚገባው የኢፌዴሪ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ በዓሉን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በዓሉ ኢትዮጵያዊን ቀድሞ የነበራቸዉን ፍቅር፣ መቻቻል፣ መከባበርና መደጋገፍን ለማጎልበት የላቀ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ቀኑ "የዕድሜ ባለጸጎችን በመደገፍ እንመረቅ" በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 18–20/ 2012 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡ የአረጋውያን ቀን በሚከበርባቸው ቀናት በተለይ በአዲስ አበባ ለአረጋውያኑ የተለያዩ ድጋፎችን በማሰባሰብ ከ10ሺህ በላይ አረጋውያንን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል፡፡ 

ከማኅበረሰቡ ባሻገር የበጎ አድራጎት ማኅበራትን በማሳተፍ ንቅናቄውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትም ይከናወናሉ ተብሏል፡፡