ድህነትን ለመቀነስ የሚሰራው የቻይና ግብረሰናይ ድርጅት በኢትዮጵያ ተከፈተ

‘ቻይና ፋውንዴሽን ፎር ፖቨርቲ አሊቬሽን’ በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ቢሮ መክፈቱን የተመለከተ መርሃግብር ተካሂዷል።

በመርሃግብሩ ላይ በኢትዮጵያ የቻይና መንግሥት ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ታን ጂያን ኢትዮጵያ ድህነትን ለመቀነስና ኢኮኖሚዋን ለማሻሻል ይፋ ያደረገችውን አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው እውን እንዲሆን የቻይና መንግሥትና ሕዝብ እንደሚደግፉት አስታውቀዋል፡፡  

ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግብን ለማሳካት የምታደርገውን ጥረትና በቅርቡ ይፋ ያደረገችውን የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር የቻይና መንግሥትና ሕዝብ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ ምክትል ፕሬዝዳንት ዋንግ ሺንዙይ በበኩላቸው ፋውንዴሽኑ ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ከሚሠሩ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባባር በትምህርት ቤት ምገባ፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦትና በሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ በ74 ሚሊዮን ብር ወጪ 27 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል።

‘ቻይና ፋውንዴሽን ፎር ፖቨርቲ አሊቬሽን’ በቀጣይ የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ኢትዮጵያ በትምህርት፣ በንጹህ መጠጥ ውሃና ሃይጅን፣ በኢኮኖሚ ዕድገት ያስቀመጠችውን ግብ ዕውን እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል።

ፋውንዴሽኑ ቢሮውን በኢትዮጵያ መከፈቱን ይፋ ባደረገበት ወቅት ‘ፓንዳ ፓክ’ ብሎ በሰየመው ግብረ ሰናይ መርሐ ግብር 43 ሺህ የደብተር ቦርሳዎች ከትምህርት ቁሳቁሶቹ ጋር ለተለያዩ አገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅቶች አስረክቧል።

ፋውንዴሽኑ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በሚያንማር፣ ኔፓል፣ ሱዳን ኡጋንዳ እና ካምቦዲያ ዘላቂ ፕሮጄክቶችን ከፍቶ እየሰራ ነው፡፡

ኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት በተያዘው ዓመት ለማክበር በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ አምባሳደሩ ጠቁመዋል። የቻይና መንግሥት ባለፉት 50 ዓመታት ከመሠረተ ልማት ግንባታና ከኢንቨስትመንት ትብብር በተጨማሪ በርካታ የሰብዓዊ ልማት ድጋፎችን ለኢትዮጵያ ማድረጉን አስረድተዋል።