የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ቅበላ ጊዜ ይፋ ተደረገ

የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ቅበላ ጊዜን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ አደረገ፡፡

ሚኒስቴሩ በ2012 የትምህርት ዘመን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሠላማዊ የመማር ማስተማር እንዲኖር የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን እንዳደረገ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በተከለሰው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረትም የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የመጀመሪያ ሴሚስቴር በአራት ቅበላ ዓይነቶች እንደሚሆን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማሪያም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ሳይንስ በመምህርነት፣ በማህበራዊ ሳይንስና በማህበራዊ ሳይንስ በመምህርነት የቅበላ ክፍል በመምህርነት የተከፈለ ነው ብለዋል፡፡

በሁለተኛው ወሰነ ትምህርት ደግሞ የመጀመሪያውን ወሰነ ትምህርት ውጤት መሠረት በማድረግ በአምስት የሙያ መስኮች ማለትም በሕግ፣ ሕክምናና የጥርስ ሕክምና፣ ፋርማሲ፣ የእንስሳት ሕክምና እና ምሕንድስና ናቸው፡፡

ሌሎቹ የትምህርት መስኮች ምደባ የሚደረገው ከአንድ ዓመት የትምህርት ቆይታ በኋላ ነው፡፡ በ‹ቪዲዮ ኮንፈረንስ› ዝግጅት ግምገማ በማድረግ የመምህራን ቅጥር እንደሚካሄድም ተጠቅሷል፡፡

አዳዲስ ፟ዩኒቨርሲቲዎችም ለተማሪ ቅበላ ዝግጁ እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የቅበላው ጊዜም ለነባር ተማሪዎች ከመስከረም 5 እስከ 25 እየተካሄደ ይገኛል፡፡ አዲስ ለሚገቡ ተማሪዎች ከመስከረም 25 እስከ 29 ቅበላው ይካሄዳል ተብሏል፡፡ ጥቅምት 03 ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ ሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት የሚያስጀምሩ ይሆናል ነው የተባለው፡፡

አዲስ ተማሪዎች በክልሉ ወይም በየወረዳው ስለመብቶቻቸውና ግዴታዎቻቸው ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ ወላጆችና ተማሪዎች በሚፈርሙት ውል መሠረት ወደ ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ፡፡

142 ሺህ 943 ተማሪዎችን የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተቀብለው እንደሚያስተምሩና የሴት ተማሪዎች ብዛት 43 ከመቶ እንደምይዝ ተገልጿል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ዝውውር የሚጠይቁት በጤና እክል ምክንያት ብቻ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

ከተፈጥሮ ሳይንስ ወደ ማኅበራዊ ሳይንስና ከማኅበራዊ ሳይንስ ወደ ተፈጥሮ ሳይንስ ዝውውር ማድረግ ይቻላል፤ ዝውውር ማድረግ የሚቻለው ግን የየመስኮቹን የማለፊያ ውጤት ሲያሟሉ እንደሆነ ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ተናግረዋል፡፡