ትናንት ምሽት በአንበሳ አውቶብስ ላይ በደረሰው የመገልበጥ አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አረጋገጠ

በትናትናው ምሽት በአንበሳ አውቶብስ ላይ በደረሰው የመገልበጥ አደጋ የ2ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ 17 ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አረጋገጠ።

በትናትናው እለት ከፈረንሳይ ለጋሲዮን ተነስቶ ወደ ለገሃር በማምራት ላይ የነበረ 55 ቁጥር አንበሳ አውቶብስ ድልድይ ውስጥ በመግባቱ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉና በ17 ሰዎች ላይም ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አረጋገጠ፡፡

የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3 አ.አ 38377 የሆነው አውቶብሱ ከፈረንሳይ ለጋሲዮን ተነስቶ ወደ ለገሃር በማቅናት ላይ ሳለ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አከባቢ በሚገኝ ድልድይ ወስጥ ነው የገባው፡፡

በአደጋው ከሞቱት 2 ሰዎች በተጨማሪ 17 ሰዎች ከባድ ጉዳት፣ 28 ሰዎች ደገሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

በሌሎች ሁለት ተሸከርካሪዎችም ላይ ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት ምክትል ኢንስፔክተር ተዘራ አብሽር ለዋልታ እንደገለጹት የአደጋው መንስኤ በመጣራት ላይ ነው፡፡

ተጎጂዎቹ በተለያዩ ሆስፒታሎች እርዳታ እየተደረገላቸው ሲሆን፤ ህክምና ተደርጎላቸው ወደ ቤታቸው የሄዱ እንዳሉም ምክትል ኢንስፔክተር ተዘራ አብሽር ተናግረዋል፡፡