ኢሬቻ የሰላም ሩጫ በአዲስ አበባ ተካሄደ

‘‘ኢሬቻ ለሰላም’’ በሚል ስያሜ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በአባቶች ምርቃት በተጀመረው ሩጫ ላይ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈውበታል፡፡

መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ባደረገው የሩጫ ውድድር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ከ15 በላይ አትሌቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በውድድሩ ከወንዶች አትሌት በሪሁ አረጋዊ እና ከሴቶች ደግሞ አትሌት ኦብሴ አብደታ የ‘‘ኢሬቻ ለሰላም’’ የጎዳና ላይ ሩጫ አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡

ለአሸናፊዎቹ የዋንጫ፣ የምስክር ወረቀት እና የ50 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በውድድሩ በወንዶች ኃይለማሪያም ኪሮስ 2ኛ ሲወጣ ደጀኔ ደበላ 3ኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡

በሴቶች ደግሞ መስታወት ፍቅሬ 2ኛ አንቻለም ሀይማኖት ደግሞ 3ኛ በመውጣት አሸናፊ ሆነዋል፡፡

በውድድሩ በሁለቱም ፆታዎች 2ኛ እና 3ኛ ለወጡ ተወዳዳሪዎች የ30 ሺህ እና የ20 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ እና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሽልማቱን ለአሸናፊዎቹ አበርክተውላቸዋል፡፡

የኢሬቻ የሰላም ሩጫ በዘንድሮው ዓመት በአዲስ አበባ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ ነው የተካሄደው፡፡