በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች ያለምንም የፀጥታ ችግር መጠናቀቃቸው ተገለጸ

በአማራ ክልል ባሕርዳርን ጨምሮ በአስር ዞኖች፣ በ47 ወረዳዎች የተካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች ያለምንም የፀጥታ ችግር መጠናቀቃቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የሚዲያ አስተባባሪ ምክትል ኮማንደር መሰረት ላቀ ለዋልታ እንደገለፁት ፖሊስ ሰልፎቹ እንደሚካሄዱ አስቀድሞ መረጃ ስለነበረውና ዝግጅት በማድረጉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቁ ረድቷል ።
ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች እና አጠቃላይ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጎን ሆነው በመስራታቸው ሰልፎቹ ያለምንም የፀጥታ ችግር ተጠናቀዋል ብለዋል።
የወንጀል መከላከል ስራ ውጤታማ የሚሆነው በህብረተሰቡ ተሳትፎ ሲታገዝ በመሆኑ ስለተደረገው ትብብር ምክትል ኮማንደሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንና ካሕናት በምዕመናን እና በቤተ ክርስቲያኗ ላይ የሚፈፀመውን ግፍ እንዲቆም የሚጠይቅ ሠላማዊ ሰልፎች በባሕር ዳር፣ ቢቸና፣ ቡሬ፣ እንጅባራ፣ መርዓዊ፣ ወልድያ፣ ፍኖተ ሠላም፣ ደባርቅ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ቆቦ፣ ማጀቴ፣ ጫጫ፣ ዋድላ፣ ዳንግላ፣ ሞጣ፣ ዳባት፣ መሐል ሜዳ፣ ውጫሌ፣ ሮቢትና፣ ላልይበላ ከተሞች አካሂደዋል፡፡