በአየር ንብረት ተጎጂ ለሆኑት ታዳጊ ሀገራት ቃል የተገባው የገንዘብ ድጋፍ በአፋጣኝ ሊደርስ ይገባል-ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

በአለም አቀፍ ደረጃ ወደ ታዳሽ ሃይል የሚደረገው ሽግግር ፈጣንና የተሳካ እንዲሆን በአየር ንብረት ይበልጥ ተጎጂ ለሆኑት ታዳጊ ሀገራት ቃል የተገባው የገንዘብ ድጋፍ በአፋጣኝ ማድረስ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ታዳሽ የሃይል ምንጮች አጠቃቀም ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረትም ለማሳካት የዘረጋችው የብሄራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን መርሃግብር መልካም ውጤት በማሳየቱ በአለም ባንክ አማካኝነት በሌሎች ታዳጊ አገራትም እየተተገበረ ነው ብለዋል፡፡

ፕሬዘዳንት ሳህለውርቅ ዘውዴ በኒውዮርክ የመጀመሪያ ቀን ውሏቸው በታዳሽ የሃይል አጠቃቀም ሽግግር ላይ አተኩሮ በመክረው ስብሰባ ማጠናቀቂያ ላይ ንግግር አድረገዋል፡፡

ኢትዮጵያ በገጠር እና በከተማ አሁን ያለውን 44 በመቶ የኤሌክትሪክ ሽፋን በአውሮፓውያኑ 2025 መቶ በመቶ ለማድረስ ብሄራዊ የኤልክትሪፊኬሽን መርኃግበር ቀርፃ እየሰራች መሆኑን ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለፀዋል፡፡

መርሃግብሩ በኢትዮጵያ ባመጣው መልካም ውጤት የተነሳም የአለም ባንክ በሌሎች ታዳጊ ሀገራት እንዲተገበር እያደረገ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ ወደ ታዳሽ ሃይል የሚደረገው ሽግግር የተሳካ እንዲሆን በአየር ንብረት ለውጥ ይበልጥ ተጎጂ ለሆኑት ታዳጊ ሀገራት ቃል የተገባው የገንዘብ ድጋፍ በወቅቱና በበቂ ሁኔታ ማድረስ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የአለም መሪዎችን በአንድ ላይ የሚያሰባስብ ትልቁ መድረክ ሲሆን ለዓለማችን አንግብጋቢ የሆኑ ርእሰ ጉዳዮች የሚመከሩበት ነው፡፡

የኒውክሌር ቅነሳ ፤ቀጣይነት ያለው ልማት እንዲሁም የአለም የጤና ጉዳይ ከዘንድሮው 74ተኛው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤው ዋነኛ አጀንዳዎች መካካል ናቸው፡፡

እንደ ኢቲቢ ዘገባ የአየር ንብረት ለውጥም በዘንድሮው ጉባኤ በትኩረት ውይይት የሚደረግበት ሌላው ርዕሰ ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል፡፡