አለምዓቀፍ የሰላም ቀን በኢትዮጵያ እየተከበረ ነው

ከአውሮፓዊያኑ 1982 ጀምሮ በአለምዓቀፍ ደረጃ የሚከበረው የሰላም ቀን በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግስታት የስብሰባ ማዕከል እየተከበረ ነው፡፡

በበዓሉ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፌሪያት ካሚል በተወካዮቻቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ከልማት አጋሮቿ ጋር በመሆን የአካባቢን ጥበቃ በማጎልበትና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ሰላሟንና ልማቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት አጋሮች ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም የኢትዮጵያን ልማትና ሰላም በመደገፍ እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች፤ የሰዎችን መፈናቀል ብሎም የልማት ተሳትፏቸውን እንደሚቀንስ ተገልጿል፡፡ ይህም የዜጎች የሰላም እጦት መነሻ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

ስለዚህም የአየር ንብረትን መጠበቅና አካባቢን ማልማት ለሰላም መጠበቅ ዋስትና ስለሚሆን ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እንዲወጣ ተጠይቋል፡፡

የዘንድሮ አለምአቀፍ የሰላም ቀን ‘‘የአየር ንብረት ጥበቃ ለሰላም’’ በሚል መሪ ቃል ነው እየተከበረ የሚገኘው፡፡