በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ስራዎች በልዩ ትኩረት እንደሚሰሩ የክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ

በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ስራዎች በልዩ ትኩረት እንደሚሰሩ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ጉባኤ ‘‘የትምህርት ጥራት ለሁለንተናዊ የሀገር ዕድገት’’ በሚል መሪ ቃል ከዞኖች እና ከተማ መስተዳድሮች ከተውጣጡ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር እየተካሄደ ነው፡፡

በጉባኤው የ2011 ትምህርት ዘመን ዕቅድ አፈፃፀም ቀርቦ ውይይት እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በክልሉ የትምህርት ጥራት ጉድለት መኖሩ ተገልጿል፡፡

በዘንድሮ የትምህርቴ ዘመን በክልሉ የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ስራዎች በልዩ ትኩረት እንደሚሰሩ የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የጎልማሶች እና ልዩ ፍላጎት ትምህርትን ለማሳደግ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

ባለፈው የትምህርት ዘመን የመምህራን እጥረት ለትምሀርት ጥራት ጉድለት ምክንያት በመሆኑ በዚህ አመት 5 ሺህ መምህራን መቀጠራቸውንም አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም የትምህርት ቤቶችን ጥራት የማሻሻል ስራ በትኩረት እንደተሰራም ተገልጿል፡፡

በፌዴራል ደረጃ የ12ኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱት 314ሺህ 853 ተፈታኞች 142 ሺህ 821 ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲ መግባታቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፣ ከኦሮሚያ ክልል 37 ሺህ 285 ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህም ከክልሉ ተፈታኞች 48 ነጥብ 9 በመቶ ማለፉን ያመለክታል ብለዋል፡፡

በጉባኤው ማጠቃለያ በ2011 የትምህርት ዘመን በክልሉ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎችና የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተቋማት የማበረታቻ ሽልማት እንደሚበረከትም ተገልጿል፡፡