የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ክህሎት ለማሳደግ የሚረዳ የ2 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት ስምምነት ተፈረመ

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ክህሎት ለማሳደግ የሚረዳ የ2 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት ስምምነት ተፈራረመ።

ፕሮጀክቱ በባህርዳር፣ ሀዋሳ፣ ጅግጅጋ፣ ጅማ፣ መቐለ እና ሠመራ ዩኒቨርሲቲዎች ይተገበራል ተብሏል።

ስምምነቱ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከህፃናት አድን ድርጅት ሴቭ ዘ ቺልድረን እና ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ዩ ኤስ አይ ዲ ጋር ተፈርሟል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም ከድርጅቶቹ ተወካዮች ጋር ተፈራርመውታል።

ፕሮጀክቱ ተቋማዊ የአቅም ግንባታ ድጋፍ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚል ለ1 አመት የሚተገበር ነው፡፡

ሚኒስትሯ በዚህ ወቅት የፕሮጀክቱን ሃሳብ አድንቀው ተመራቂ ተማሪዎችን የስራ ገበያው የሚፈልገው አይነት ክህሎት ይዘው እንዲወጡ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

አያይዘውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለትምህርት ጥራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በስምምነቱ ዩኒቨርሲቲዎቹ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር በትምህርት በሚገኙ ክህሎቶችና የስራው ዓለም በሚፈልጋቸው ችሎታዎች መካከል የሚኖርን ያለመጣጣም ችግር ለመቅረፍ ይሰራሉ ተብሏል። (ምንጭ፡-የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር)