በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራበት ነው- ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ

ኢትዮጵያ የምግብ እና ስርዐተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው የልማት ተግባራት አንዱ በማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት መሆኑን ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ በህጻናት ላይ የሚታየውን የመቀንጨር ችግር ለመፍታት የተቀረጸው የሰቆጣ የውሳኔ ሃሳብ ላይ የሚመክረው ጉባኤ በኒውዮርክ ተካሂዷል፡፡

በዚህ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እንዳሉት ኢትዮጵያ ባለፉት 16 አመታት የህጻናት መቀንጨርን በ20 በመቶ መቀነስ ችላለች፡፡

ከአንድ አመት በፊት የጸደቀው የምግብና የስርዐተ ምግብ ፖሊሲ መቀንጨርን ለመከላከል የተቀረጸውን የሰቆጣን የውሳኔ ሀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ቁልፍ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም ከሁሉም አጋሮች ጋር ተባብሮ ለመስራት ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት የገለጹት ፕሬዝደንት ሣህለወርቅ፣ አጋር አካላትም ድጋፋቸውን የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በስብሰባው ላይ የተሳተፉት አጋሮች በበኩላቸው፣ እስካሁን የተገኘው ውጤት አበረታች መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡ በቀጣይም በሰቆጣ የውሳኔ ሀሳብ ላይ የተቀመጡት ግቦች እንዲሳኩ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ 38 በመቶ የሚሆኑት ህጻናት የመቀንጨር ችግር እንደሚያጋጥማቸው ከፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡