“አንድነታችንንና ሰላማችንን የጋራ ሃብታችን አድርገን እንጠብቅ” – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በደመራ በዓል ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

‹‹የጎደለውን ፍቅር እና ሠላም፣ አንድነት እና እኩልነት፣ ፍትሕ እና ወንድማማችነት በመስቀሉ ውስጥ ተትረፍርፎ እናገኘዋለን›› ያሉት አቡነ ማቲያስ ይቅርታና መተባበር፣ መከባበር እና መተባበር በመስቀሉ ሥር ስለሚገኙ ለእነዚህ ፍላጎቶች የመስቀሉን ጥያቄዎች መመለስ ግድ እንደሚል አሳስበዋል፡፡

‹‹የቤተ ክርስቲያን ጥያቄዎች ካልተመለሱ ምኞቶች ሁሉ ቅዥት ከመሆን በቀር ሊሳኩ አይችሉም›› ብለዋል፡፡ በአንድነትንና ሠላምን የጋራ ሀብት አድርጎ ለሁሉም የምትበጅ ሀገር እንድትኖር መሥራት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡ 

ብፁዕነታቸው በመልዕክታቸው የኢትዮጵያውያን የጋራ ሀብት የሆነውን ሰላም እና አንድነት መጠበቅ ይገባል ብለዋል፤ የቤተ ክርስቲያን ግብረ አድኅኖ ፍጹም እንደሆነና ቅዱስ መስቀልም የሰው ልጆች የድኅነት ምልክት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡  

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በሀገሪቱ ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈፀሙ ያሉ በደሎችን በፅኑ አውግዘዋል፡፡ ‹‹የመስቀሉ ነገረ ድኅነት በአንድ ጊዜ ተሠርቶ የተጠናቀቀ አይደለም፤ የተጣሉትን ያስታረቀ በአንድ መዓድ የሚያስቀምጥ፣ ሠላምና ፍቅርን የሚያድል አምላካዊ ምስጢር ነው›› ብለዋል፡፡

አቡነ ማቲያስ እንደገለጹት ቀደምት ኢትዮጵያውያን ነገረ መስቀሉን በትክክል ተግብረው በዓለም ብቸኛ የሆነ ነፃነት እና አንድነትን ለትውልድ አስረክበዋል፡፡ ‹‹ይህንን እውነት ትቶ ቤተ ክርስቲያንን እያቃጠሉ ልማትን ማምጣት አይቻልም፡፡ መስል ድርጊቶች በአስቸኳይ እስከ መጨረሻው መቆም አለባቸው›› ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ሊቀ ጳጳሱ “በዚህ ዙሪያ የተፈጠረ ነገር ሁሉ መግባባት አያደርስም፤ መስቀልን ይሳለሙታል እንጂ አያቃጥሉትም፤ ኢትዮጵያውያን አበው መስቀልን አክብረው ይሰግዱለታል እንጂ አይረግጡትም፤ አያዋርዱትም” ብለዋል፡፡ በመስቀሉ እና በቃሉ ክብራቸውን እና ደኅንነታቸውን እንዳገኙበትም ተናግረዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ‹ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ ልታገኙት አትችሉም፤ ትጣላላችሁ፣ ትዋጋላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም› ሲል ያስቀምጣል’ ምኞት ሁሉ ሊሳካ ያልቻለው ከመስቀሉ እየተራቀ በመሄዱ ነው›› ብለዋል፡፡

ሊቀ ጳጳሱ የነብዩ ኢሳያስ አስተምህሮንም አበይት ርዕስ አድርገው አቅርበዋል፡፡ ‹‹እናንተም ዳር ዳር ትሄዳላችሁ፤ እኔም ዳርዳሩን እሄዳለሁ›› የተባለው በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጸመ እንደሆነም በመልዕክታቸው አንስተዋል፡፡