የባህል መድሃኒት ጥናትና ምርምር ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆነ

አገር በቀል የመድሃኒት ህክምና እውቀትን በመሰነድ፣ በመጠበቅ እና የተጠናከረ ጥናትና ምርምርን በማከናወን የባህል ህክምናን ለማሳደግ ይረዳል የተባለው የኢትዮጵያ የባህል መድሃኒት ጥናትና ምርምር ፍኖተ ካርታ ዛሬ ይፋ ተደረገ፡፡   

በባህል መድሃኒት ጥናትና ምርምር ፍኖተ ካርታ ዙሪያ የተለያዩ ባለድርሻ ተቋማት እና ከአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ የባህል ሐኪሞች በተገኙበት በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለሶስት ቀናት የሚቆይ ምክክር እየተካሄደ ነው።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን ፍኖተ ካርታውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ፍኖተ ካርታው የባህል ህክምናውን በሳይንሳዊ ምርምሮች በመደገፍ፣ ጠቀሜታውን በማጎልበት፣ የጎንዮሽ ጉዳቶችን በመቀነስ እና ከዘመናዊ ህክምና ጋር ለማቀናጀት ያለመ ነው።

የባህል ሕክምና ኢትዮጵያ ካሏት እምቅ ሐብቶች አንዱ ቢሆንም እስካሁን ብዙ እንዳልተሰራበት ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ህክምናውን ከመደበኛ ትምህርት ጋር በማቀናጀትና ለባህል ሕክምና የሚሆኑ እንስሳትንና እፅዋትን በማሰባሰብ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ሥራ ለማከናወን የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ከመድሐኒት አምራቾችና የባህል ሕክምና አዋቂዎች ጋር በመስራት የባህል ሕክምና ጥራትና ደረጃን በማጎልበት ፈዋሽነታቸው ላይ ትኩረት ይደረጋል ተብሏል፡፡  

የባህል ህክምና አዋቂዎች በበኩላቸው ለረጅም ዓመታት ተሳቀው ይሰሩ እንደነበር ገልጸው፣ ፍኖተ ካርታው መዘጋጀቱ በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት የሚያስችል እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ፍኖተ ካርው መዘጋጀቱ ለሀገር በቀል ህክምና የሚሰጠውን ትኩረት እንደሚያሳድገውና ለህክምና ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬም እንደሚቀንስ ገልጸዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው ይፋ በተደረገበት ጊዜ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና የባህል አዋቂዎች ማህበር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ካለው የባህል ሕክምና አገልግሎት 80 በመቶ የሚሆነው ለሰዎች አገለግሎት እንደሚውልና 90 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ለእንስሳት ህክምና እንደሚውል በመድረኩ ተገለጿል፡፡