በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓልን ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ

መስከረም 24 እና 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ የሚከበረው የሆራ-ፊንፊኔ እና ሆራ ሃር-ሳዲ የኢሬቻ ክብረ በዓልን ከዋዜማው ጀምሮ በደማቅ ስነስርዓት ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

ባህላዊ ፌስቲቫሉን በአንድ በኩል የህዝቦች ትስስር ተምሳሌት በሌላ በኩል ደግሞ በቀጣይ የኢሬቻ ፌስቲቫል የሰላምና የአንድነት በዓል አድርጎ በማክበር ለሃገሪቱ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰትን እንዲጨምር ታስቦ እየተሰራበት መሆኑም ተገልፃል፡፡

የልምላሜ ምልክት፣ የመልካም ምኞት መገለጫም ተደርጎ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በፍስሃ እና ፍቅር ተመስሎ ይከበራል፡፡ በዚህ ስፍራ ስለህብረት እና አንድነት አብዝቶ ማዜም፣ ማወደስ በጉልህ ይስተዋላል፡፡

ፖለቲካን ከባህል፤ የህዝብ አስተዳደርንም ከፈርሃ ፈጣሪ አጣምሮ የያዘው የገዳ ስርዓት አንዱና ዋነኛ መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል በህዝቡ ዘንድ ያለምንም ሃይማኖታዊ ብሎም ፖለቲካዊ አመለካከት ደምቆ እየተከበረ፤ ከትውልድ ትውልድም ሲወርድ ሲዋረድ እንደመጣ ይነገራል፡፡

በዓሉን በባለቤትነት የሚመራው የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮም ዘንድሮ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ከድፍን ምዕተ አመትም ለዘለለው ጊዜ ተቋርጦ የቆየውን የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ ፊስቲቫልን ዳግም የሚያስጀምር በመሆኑ ሰፋፊ ዝግጅቶች መደረጋቸውን በሰጠው መግለጫ አብራርቷል፡፡

በዓሉ ሲከበርም እንዲሁ ህዝብ ተሰባስቦ የሚበተንበት ሳይሆን የእሬቻን እሴት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የህዝቦች ትስስር ማጠናከሪያ ገመድ እንዲሆንም መወጠኑ ነው የተጠቆመው፡፡

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊው አቶ ግርማ ኃይሉ ለመገናኛ ብዙሃኑ በሰጡት መግለጫቸው ከወትሮ ከፍ ባለ ዝግጅት ሊደረግ በመሰናዶ ላይ ያለው የዘንድሮ ኢሬቻ ክብረ በዓል ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ሚና ውስጥ ጠብታ ውሃን የሚጥል ለመሆኑ በባህላዊ ልብሶች ዘርፍ የተፈጠረውን የባህል ልብስ ገበያን እንደአመላካች ነጥብ ተጠቅሷል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ወደ መዲናይቱ ሲመጣም የሚፈጠረው የገበያ እድል ብቻ ሳይሆን የበዓሉን አኩሪ እሴት ለህዝቦች ለማስተዋወቅ ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር ታምኖበት ነው፡፡

የኢሬቻ ፌስቲቫል አንዱ አካል የሆነው በበዓሉ እሴት ላይ ያጠነጠነ፣ የመንግስት የስራ ሃለፊዎችና ምሁራን አንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፈው ኮንፌረንስ ሃሙስ መስከረም 22 ይካሄዳል፡፡ ፎረሙም በሃገሪቱ እና በመላው ዓለም ያለው የኦሮሞ ህዝብ ባለበት ሁሉ የገዳ ስርዓትና እሬቻን ማክበር ባለበት አግባብ ላይ ይመክራል፣ ወደፊት ለሚከበረው የኢሬቻ በዓለም አቅጣጫን ይጠቁማል፡፡ መስከረም 23 በእለተ ዋዜማም ከቀኑ 8 ሰዓት አስከ 12 ሰዓት በመስቀል አደባባይ የተሰናዳውን ዝግጅት ጨምሮ የተለያዩ ባህላዊ ትርዕቶች እና የኦሮሞን ባህል ማስተዋወቅና የአንድነትንም ጥሪ ያስተላልፋል የተባለለት ኮንሰርት ይደረጋል፡፡

መስከረም 24 በበዓሉ እለትም እሬቻ ሰላማዊ እና የፍቅር በዓል መሆኑን ለዓለም ሁሉ ለማሳት ይረዳ ዘንድ፤ መልዕክት የሰፈረበት 5 ሚሊየን ነጭ ባነዲራ ተዘጋጅቷል፡፡ በአዘጋጅነቱ የመሪነት ሚናን እየተወጣ ያለው የአአ ከተማ አስተዳደርም የእሬቻ እንግዶቹን ለመቀበል ዝግጅት ማጠናቀቁም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ ከሃገር ውጭ በበዓሉ ለመሳተፍ ጥያቄ ያቀረቡ አሉ፡፡ በሃገር ቤት ከኦሮሚያ ክልል ውጭ የበዓሉ ተሳታፊ የሚሆኑ ከተለያዩ ክልሎች ወደ አአ የሚመጡ እንግዶችንም ለመቀበል በአራቱም አቅጣጫ ዝግጅት ተደርጓል፡፡