ዩኒቨርስቲዎች የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የልህቀት ማዕከላት ለመሆን ቆርጠው መስራት ይገባቸዋል- ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም

ዩኒቨርስቲዎች የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የልህቀት ማዕከላት ለመሆን ቆርጠው መስራት እንደሚገባቸው ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም አሳሰቡ፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም በትናንትናው ዕለት የአክሱም ዩኒቨርስቲን ጎብኝተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ላለፉት ሁለት ቀናት በአክሱም ዩኒቨርስቲ ሲያደርገው የነበረውን ግምገማ ሲያጠናቅቅም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም በዩኒቨርስቲው በመገኘት ጉብኝትና ከስራ አመራር አካላት ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ፕሮፌሰር ሂሩት እንዳሉት ዩኒቨርስቲዎች የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የልህቀት ማዕከላት ለመሆን ቆርጠው መስራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

አያይዘውም አክሱም ዩኒቨርስቲ ቀጣዩን ዓመት ሰላማዊ ለማድረግ ከአከባቢው ማህበረሰብና በዙሪያው ካሉ አጋሮች እንዲሁም ከከተማው የፀጥታ መዋቅሮች ጋር ተቀናጅቶ መስራት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በተለይ የተባረሩ ተማሪዎችም ሆኑ ሌሎች ወደ ዩኒቨርስቲው ሾልከው እንዳይገቡ በዩኒቨርስቲው መግቢያ በር ላይ የጣት አሻራ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ቁጥጥር ማድረግ መጀመሩንም አድንቀዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ከነዚህም መካከል የውሃና መብራት እንዲሁም የኢንተርኔት መቆራረጥ ችግሮች ይገኙበታል፡፡

ፕሮፌሰር ሂሩት ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የችግሮችንም መፍትሔ ሊያመነጩ ይገባል ብለዋል፡፡

ለምሳሌ ያህልም የአካባቢውን የውሃ ችግር የሚቀርፉ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉ መንገዶችን ማመላከት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጸሐዬ አስመላሽም ሰላማዊ መማር ማስተማር ለማስፈን የተለያዩ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታውን ገልጸው የውሃ አቅርቦት፣ የኢንተርኔትና የመብራት መቆራረጥ እንዳይኖር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው በአሁኑ ጊዜ ነባር ተማሪዎችን እየተቀበለ እንደሆነ የገለፁት ፕሬዝዳንቱ 2012 የትምህርት ዘመንን ፍፁም ሰላማዊ ለማድርግ ከከተማው ነዋሪዎች እና ከሚመለከታው የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡ (ምንጭ፡-የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር)