የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለፀ

የ2011 ዓ.ም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃግብር የማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ አገልግሎቱን ለማጠናከር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በጎ ፈቃድ ማለት ከያገባኛል ስሜት የሚመነጭ የሰብአዊነት መርህ ተግባራዊ የሚደረግበት አገልግሎት ነዉ ብለዋል፡፡

መንግስት የወጣቶችን ችግር ለመፍታት የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን አፈጉባኤው ጠቁመዉ፣ ለዚህም የበጎ ፈቃድ ሚናን ለማጎልበት ለዘርፉ አስፈላጊዉ ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ወጣቶች የአገር አንድነትን ለማስቀጠል በስነ ምግባር የታነፁ፣ ራዕይ ያላቸዉና ጠንካራ የስራ ባህልንም ሊያዳብሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ በበጀት አመቱ ዉጤታማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላከናወኑ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት የሽልማትና ዕዉቅና መስጠት ስነ ስርአት ተከናዉኗል፡፡

በ2011 ዓ.ም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር የ1ሺህ 441 አቅመ ደካሞች ቤቶች ታድሰዋል፡፡       

ከ2002 እስከ 2011 ዓ.ም ከ92 ሚሊየን በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፈዋል፡፡