ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ በሃይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት ሳይለያይ አንድነቱን የሚያሳይበት በዓል ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ በሃይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት ሳይለያይ አንድነቱን የሚያሳይበት በዓል ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለበዓሉ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ለኦሮሞ ህዝብ ምስጋና ለሚቀርብበትና፣ የፍቅር፣ አንድነት፣ ይቅርታና የእርቅ መገለጫ ለሆነው የኢሬቻ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

በዓሉ የኦሮሞ ህዝብ ሰማይና ምድር፣ ወንዞችና ሐይቆች፣ ክረምትና በጋ፣ ሌሊትና ቀን፣ ሕይወትና ሞትን ለፈጠረው ፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት ቀን ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የኢሬቻ በዓል የፈጣሪና ፍጥረታት ግንኙነት የሚንጸባረቅበት በዓል ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት፡፡

ኢሬቻ በመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተመዝግቦ ያለው የገዳ ስርዓት አካል ሲሆን፣ ገዳ ስርዓት ከስርዓትነትም አልፎ ዘመናዊ የአመራር ስልትን ለዓለም ያበረከተ ነው ብለዋል፡፡

የገዳ ስርዓት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የሚደረግበት ሲሆን፣ የስልጣን ዘመን በአግባብ ከተመራ በኋላ የስልጣን ሽግግሩ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ በመግባባትና በመረዳዳት የሚከናወን መሆኑን ዶ/ር ዐቢይ ገልጸዋል፡፡

“ዛሬም ለችግራችን መፍትሔ የሚሆነው ወደ ቀደመው ባህላችን ተመልሰን ከዘመናዊ ስርዓት ጋር በማስተሳሰር የገዳ ስርዓትም መጠቀም ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡