በቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት የተገነባው የቁስቋም ብርሃን የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከል ተመረቀ

በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት በ12 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የቁስቋም ብርሃን የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከል ዛሬ ተመረቀ፡፡

ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ የቁስቋም ብርሃን የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከል ግንባታ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በአጭር ጊዜ በመጠናቀቁ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡

መሰል የበጎ አድራጎት ስራዎችን መስራት ለሚፈልጉ አካላት ጽህፈት ቤታቸው ክፍት መሆኑን በመግለፅ  ጽህፈት ቤቱ የጀመራቸውን ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የካቲት 29 ቀን በቁስቋም የህፃናት ማሳደጊያ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸው ይታወሳል፤ ከስድስት ወራት በኋላ የቁስቋም ብርሃን የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከልን ለዘውዲቱ መሸሻ የህጻናት ማሳደጊያ አስረክበዋል፡፡

ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ለ250 ህጻናት እናት ሆነው ሲያሳድጉ የነበሩት የዘውዲቱ መሸሻ የህፃናት ማሳደጊያ መስራች ወ/ሮ ዘውዲቱ መሸሻ በበኩላቸው ለተደረገላቸው መልካም ስራ አመስግነዋል፡፡

በምርቃት ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በከተማዋ ውስጥ ለሚሰራቸው ስራዎች ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የቁስቋም ብርሃን የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከል ከ90 በላይ ህጻናትንም ማስተናገድ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት እስከአሁን 20 ትምህርት ቤቶች በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡