የኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ በድምቀት ተከበረ

የኢሬቻ በዓል ከንጋት 11 ሰዓት ጀምሮ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል፡፡

በዓሉ በሆራ አርሰዴ በአባገዳዎች ምርቃትና የምስጋና ስነስርዓት ነው የተጀመረው፡፡

ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመምጣት በስፍራው የተገኙ አባቶች፣ እናቶች፣ ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች የምስጋና ስነስርአት አድርሰዋል።

የሲዳማ እና ሃላባ ወጣቶችም ታድመው በስፍራው በመገኘት የየባህላቸውን መገለጫዎች አሳይተዋል።

ከንጋቱ 11 ሰዓት በተጀመረው ፕሮግራም በተለያዩ መርሃ ግብሮች አባ ገዳዎችና ከተለያዩ አካባቢዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ኢሬቻ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበር ሲሆን፣ በበጋ ወቅት በከፍታ ቦታ ላይ የሚከበር ወይም ኢሬቻ ቱሉ እንዲሁም በጸዳይ ወቅት መግቢያ ላይ በወንዝ ዳር የሚከበረው ወይም ኢሬቻ መልካ በመባል የሚታወቅ ነው፡፡

በዛሬው ዕለት በቢሾፍቱ የተከበረው ኢሬቻ መልካ የኦሮሞ ህዝብ የክረምት ወቅት ማለፉንና የጸደይ ወቅት መምጣቱን አስመልክቶ ለታና አደይ አበባን በመያዝ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት በዓል ነው፡፡

ትላንትና በአዲስ አበባ በዓሉ በተመሳሳይ ሁኔታ በድምቀት ተከብሮ ማለፉ ይታወቃል።