ሙዚቀኛ ኤሊያስ መልካ ተሸኘ

የሙዚቀኛ ኤሊያስ መልካ የስንብት መርሃ ግብር በዛሬው እለት በብሄራዊ ቴአትር ተካሂዷል።   

በመርሃ ግብሩ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዩን ጨምሮ ቤተሰቦቹ፣ የሙያ አጋሮቹ እና አድናቂዎቹ በተገኙበት ተካሂዷል።

ኤልያስ የሙዚቃ አቀናባሪ፣ የዜማና ግጥም ደራሲ፣ ጊታርና ፒያኖ ተጫዋች ሲሆን፥ አዳዲስ ሙዚቀኞችን ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ አስተዋውቋል።  

ከያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ቼሎ የሙዚቃ መሳሪያን ተምሮ ከጨረሰ በኋላ ከመምህሩ አክሊሉ ዘውዴ፣ ከእዝራ አባተ ከያሬድ ተፈራና ከሌሎችም ጋር በመሆን በመዲና ባንድ ውስጥ ሰርቷል።

በተጨማሪም ከመሃሙድ አህመድ፣ ከፍቅርአዲስ ነቃጥበብ፣ ከአለማየሁ እሸቴ፣ ቴዲ አፍሮ፣ እዮብ መኮንን፣ ሚካኤል በላይነህ፣ ዘሪቱ ከበደ፣ ልኡል ሀይሉ፣ ሀይሌ ሩትስ፣ ሚካያ በሃይሉ፣ ትግስት በቀለ፣ ቤሪ እና ዳን አድማሱ ጋር አብሮ በመስራት በሙያው አሻራውን አኑሯል፡፡

ከዜማ ላስታስና ከአፍሮ ሳውንድስ ባንዶች ጋርም የሰራበት ጊዜ ነበር። ኤልያስ ከ40 በላይ ሙሉ አልበሞችን አቀናብሯል። ሙዚቀኛ ኤልያስ መልካ የስኳር እና ኩላሊት ህመም ገጥሞት ህክምናውን የቆየ ቢሆንም ሕመሙ ተባብሶበት ባሳለፍነው ቅዳሜ መስከረም 24/2012 ዓ.ም በሆስፒታል ህይወቱ እንዳለፈ ታውቋል፡፡

ዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት በሙዚቀኛ ኤልያስ መልካ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት የተሰማውን ትልቅ ሀዘን እየገለፀ፥ ለቤተሰቦቹ፣ ለሙያ ጓደኞቹ እና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል።