ከአዕምሮ ጤና ችግር አምራች የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ለመጠበቅ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

የአዕምሮ ጤና ችግር በከፍተኛ ሁኔታ እያጠቃው የሚገኘውን አምራች የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ከችግሩ ለመጠበቅ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን ዘንድሮ “ትኩረት ራስን ማጥፋትን ለመከላከል” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው።

የአዕምሮ ጤና የሚያስከትሉ ችግሮች እንዳሉ ሆነው በሕሙማኑ ላይ የሚደረገው ማግለል እና መድሎ ችግሩን አሁንም ከባድ አድርጎታል ተብሏል።

አለማችን በተለያዩ ክስተቶች ከምታስተናግዳቸው ሞት በአዕምሮ ህመም ምክኒያት ራሳቸውን የሚያጠፉት 78 በመቶውን እንደሚይዝና ከዚህ ውስጥ 50 በመቶዎቹ ደግሞ እድሜያቸው 15 እስከ 44 ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ተላላፊ በሽታ ያልሆነው የአዕምሮ ህመም፤ በኢትዮጵያ ራስን በማጥፋት ረገድ ከሳሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደትቀመጥ አድርጓታል ነው የተባለው፡፡

የአዕምሮ ህመም በአማካይ እድሜን በ30 አመት እንደሚቀንስ ጥናቶች የሚያመለክቱ ሲሆን፣ እንደ ኢትዮጵያም 27 ሚሊዮን ዜጎች ከአዕምሮ ጋር በተያያዘ የባለሞያ እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የአለም ጤና ድርጅት በአውሮፓዊያኑ 2030 ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መቀነስ ላይ ትኩረቱን አድረጎ እየሰራ ሲሆን፣ ራስን ማጥፋት አንደኛው ነው፡፡

በቅዱስ አማኑኤል የአዕምሮ ህክምና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል  የአዕምሮ ህክምና ሳይካትሪስት የሆኑት ዶ/ር መሀመድ ንጉሴ ራስን ለማጥፋት መንስኤ የሆነውን የአዕምሮ ህመም አስመልክቶ አበረታች እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

በአለምዓቀፍ ደረጃ አስሩ የአዕምሮ ህሙማን መካከል አንዱ ብቻ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እንደሚያገኝ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡