በቤተ መንግስት ግቢ የተሰራው የአንድነት ፓርክ በይፋ ተመረቀ

የመደመር እሳቤ ማሳያ እንደሆነ የተገለፀው የአንድነት ፓርክ በታላቁ ቤተመንግስት የምስራቅ አፍሪካ መሪዎች በተገኙበት በይፋ ተመርቋል፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ በብሄራዊ ቤተ መንግስት ግቢ በሚገኘው የአንድነት ፓርክ ምረቃ ስነስርዓት ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የገቡት የኬኒያው ፕሬዘዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ፣ የኡጋንዳው ፕሬዘዳንት ዮሪ ሙሶቬኒ፣ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሙሃመድ አብዱላሂ ሙሃመድ፣ የደቡብ ሡዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ማያርዲት እና የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ አምዶክ ተሳትፈዋል፡፡

በተጨማሪም አምባሳደሮች፣ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች እና ከተለያየ መስሪያ ቤት የተጋበዙ በርካታ እንግዶችም ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ያለፉ ታሪካዊና ማህበራዊ እሴቶች እየተዘከሩና ለመጪው ትውልድ እየጎለበተ እንድሄድ ሁሉም ታሪኩን እንዲጎበኝ በማሰብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ሃሳብ አመንጪነት በታላቁ ቤተ መንግስት የተገነባው የአንድነት ፓርክ የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት ረገድም ጉልህ ሚናን ይጫወታል ተብሎ ታምኖበታል።

የአንድነት ፓርክ ለጋራ ግብ በአንድነት በመቆም የፍፃሜውን ምዕራፍ ዘመን ተሻጋሪ በሆነ የሕብረት አቅም ማጠናቀቅ የመቻል ተምሳሌት እንደሆነ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ በግዝፈቱ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ባይመስልም፤ በተያዘለት አጭር ጊዜ እውን መሆኑ ይበል አሰኝቷል፡፡

በታላቁ ቤተመንስት ማምሻውን በተካሄደ ስነ-ስርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የአንድነት ፓርክ እውን እንዲሆን እንዲሁም ሀገራዊ ለውጡ እንዲሳካ ድጋፍ እያደረጉ ለሚገኙ ተቋማትና አካላትና ግለሰቦች እውቅና እንዲሁም ሜዳሊያ ሰጥተዋል፡፡

በዝግጅቱ ንግግር ያደረጉት የኡጋንዳው ፕሬዘዳንት ዮሪ ሙሶቬኒ የአንድነት ፓርክ ትክክለኛ የአመለካከት ለውጥ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህን ሀሳብ ላመነጩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ እና የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ንግግር አድርገዋል፡፡

ያለፉትን ታሪካዊና ማህበራዊ እሴቶቻችን እየዘከርንና ለመጪው ትውልድ እያጎለበትን እንሂድ በማለት የጋበዘው የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት፤ ከሰኞ ጥቅምት 3 ፣ 2012 ዓ.ም ጀምሮ ህብረተሰቡ 200 ብር በመክፈል ፓርኩን እንዲጎበኝ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በተጨማሪም 1 ሺህ ብር በመክፈል በአስጎብኚ በመታገዝ በቪአይፒ ትኬት ቤተ መንግስቱን መጎብኘት እንደሚቻልም ነው የተገለፀው፡፡

የጉብኝቱ መርሃ ግብሩ በይፋ ሲከፈትም የመከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በቤተ መንግስት ግቢ የተሰራውን የአንድነት ፓርክ ይጎበኛሉ ተብሏል፡፡

ቅዳሜ እና እሁድ የእድሜ ባለፀጎች እና የጎዳና ተዳዳሪዎች ቤተ መንግስቱን እንደሚጎበኙ ተነግሯል።

በቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ የተሰራው አንድነት ፓርክ በ40 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ ለግንባታው 5 ቢሊየን ብር ወጪ ጠይቋል፡፡