ዓለም አቀፍ የእይታ ቀን እየተከበረ ነው

ዓለም አቀፍ የእይታ ቀንን በማስመልከት በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚገኙ ተማሪዎች ነፃ የዓይን ምርመራና ሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡

ቀኑን በማስመልከት በግላኮማ፣ ትራኮማ እና የዓይን ግርዶሽ በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ የዓይን ህክምና ባለሙያዎች በተገኙበት በትምህርት ቤቱ ውይይት እየተደረገ ነው፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዕለቱ ተገኝተው እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የዓይን ብርሃናቸውን ከሚያጡት 80 በመቶ የሚሆኑት በወቅቱ ባለመመርመራቸውና በአግባቡ ሕክምና ባለመውሰዳቸው መዳን እየቻሉ ለዓይነ ስውርነት እየተጋለጡ ነው፡፡  

የጤና ሚኒስቴር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በትምህርት ቤቶች የምርመራ የንጽህና አጠባበቅ ሥልጠናዎችን በመስጠት ለዓይን ብርሃን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ዶክተር ሊያ አክለው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ችግሩን ለመቅረፍ እንዲቻል በ2011 ዓ.ም ለ80 ሺህ ዜጎች የአይን ሞራ ግርዶሽ ገፈፋ፣ ለ610 ሺህ ያህሉ ደግሞ የትራኮማ ህክምና አገልግልት መሰጠቱ ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ 330ሺህ ያህሉ ሕክምናውን ለመውሰድ እየተጠባበቁ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የዓይን ሞራ ግርዶሽ 50 በመቶ፣ ትራኮማ 11 በመቶ እንዲሁም 5 በመቶ ያህል ዜጎች በግላኮማ ህመም እንደሚጠቁና ችግሩን ለመቅረፍ እንዲቻል ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የነፃ የዓይን ምርመራና ሕክምና አገልግሎቱና ውይይቱ አስከ ነገ ድረስ “ለእይታችን ቅድሚያ እንስጥ!” በሚል መሪ ሐሳብ እየተከበረ እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡