የዓለም ምግብ ቀን ለ39ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ተከበረ

የዓለም ምግብ ቀን ለ39ኛ ጊዜ "የዛሬ ጥረት ለነገ ስኬት" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ተከብሯል፡፡

በዓሉ በአዲስ አበባ በተከበረበት ወቅት፤ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተጋላጭ መሆኑ ተገልጿል፡፡ 

በዓለም ላይ ከ800 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ለምግብ እጥረት ተጋላጭ መሆናቸውም በዚሁ ወቅት የተገለጸ ሲሆን፤፣ ችግሩን በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2030 ከዓለም ለማስወገድ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ከኢትዮጵያም የምግብ እጥረት ችግርን ለመቅረፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብና ስነ-ምግብ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ መንግስትና በዘርፉ የሚሰሩ አጋር አካላት በጋራ እየሰራ እንደሆነ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የግብርና ሚኒስትር አማካሪ ዶ/ር ኢያሱ አብርሃ ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ የሚታየውን የምግብ እጥረት ለመቀነስና የተመጣጠነ ምግብን ተደራሽ በማድረግ ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር በዋናነት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ዶ/ር ኢያሱ ገልጸዋል፡፡

በገጠር አካባቢ የሚታየውን የምግብ እጥረት ችግር ለመቅረፍ በአርሶአደሩ የሚያመርተውን ምግብ እንዲመገብ ለማድረግ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንደሚሰራም አክለው  ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ተወካይ ወ/ሮ ፋጡማ ሰይድ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የሚታየውን የምግብ እጥረት ችግር ለመቅረፍ መንግስት ብቻ ሳይሆን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተጀመረው የትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራም ችግሩን ለመቅረፍ የበኩሉን እስተዋጽኦ እንደሚያበረክትና መሰል ፕሮግራሞች በተለያዩ ቦታዎች ተግባራዊ ቢሆኑ ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻል የበዓሉ ታዳሚዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የዓለም የምግብ ቀን ለ39ኛ ጊዜ ሲሆን፤ በዓሉ "የዛሬ ጥረት ለነገ ስኬት" በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡