ኢትዮጵያ በ2025 ከካርበን ልቀት ነፃ የሆነ የአረንጓዴ ልማት ስራ ለማከናወን ማቀዷን ገለጸች

ኢትዮጵያ በአውሮፓውያን ጊዜ አቆጣጠር በ2025 ከካርበን ልቀት ነፃ የሆነ የአረንጓዴ ልማት ስራ ለማከናወን ማቀዷን የውሃ፣ መስኖና ኢኔርጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የውሃ፣ መስኖና ኢኔርጂ ሚኒስቴር እና በፊንላንድ መንግስት በጋራ ባካሄዱት የውይይት መድረክ ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪካ በከባቢ አየር ብክለት ላይ ያላቸው ሚና በጣም ውስን ቢሆንም በከባቢ አየር ለውጥ ምክንያት እየደረሰባቸው ያለው ችግር ግን ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የውሃ፣ መስኖና ኢኔርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጀነር ስለሺ በቀለ የአየር ብክለትን የሚያምቅ አቅም ወይም አሰራር ባለመኖሩ በኢትዮጵያ በ2025 የካርቦን ልቀቱ ዜሮ የሆነ የአረንጓዴ ልማት ስራ ለመስራት መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡ አሁን ላይ ኢትዮጵያ 97 በመቶ ከታዳሽ ኃይል እያመነጨች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የፊንላንዱ ፕሬዝዳንት ሳውሊ ኒኒስቶ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ላይ እየሰራች ያለችው ስራ ለሌሎች ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አክለውም የዓለም ህዝቦች በከባቢ አየር ብክለት ምክንያት ከባድ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ ቅፅበታዊ ለሆነው ችግር ቅፅበታዊ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችው እንቅስቃሴም ሌሎቹን የሚያበረታታና የመሪነት ሚናን የሚያሳይ ነው፤ ፊንላንድም እስከ ፈረንጆቹ 2030 የካርበን ልቀትን ለመቀነስ እየሰራች ነው ብለዋል፡፡

ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ የምድር ሙቀት በአማካኝ በ1 ነጥብ 62 ድግሪ ፋራናይት ጨምሯል፡፡ በተለያዩ የዓለም ሀገራት እየተፈጠረ ያለው የበረዶ መቅለጥ፣ ሰደድ እሳት፣ አውሎንፋስን ያዘለ ከባድ ዝናብና ሌሎቹም ጉዳቶች ማሳያዎች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡