አማራ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች ከፍተኛ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንደሚካሄድባቸው ጥናት አመለከተ

አማራ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች ከፍተኛ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንደሚካሄድባቸው ጥናት አመለከተ፡፡

በኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት ለመውጣት በሚያደርጉት ጥረት ለችግር እየተዳረጉ እንደሆነ ጥናት አመላክቷል፡፡

ችግሩን ለመከላልም በህገ ወጥ መንገድ ድንበርን የማሻገር ወንጀልን የተመለከተውን አዋጅ ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታውቃል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የችግሩን አሳሳቢነት የጋራ ለማድረግና መፍትሄዎችን ለማመላከት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የሰዎች ንግድን እና በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን በተመለከተ አዲስ አበባ ላይ ምክክር አድርጓል፡፡ ዓለም አቀፍ የሰዎች ዝውውር ሁኔታን የዳሰሰ የመነሻ ጽሁፍ ላይም ውይይት ተደርጓል፡፡

በተለይ በኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ለመውጣት በሚያደርጉት ጥረት ለችግር እየተዳረጉ እንደሆነ ጥናቱ አሳይቷል፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ፀረ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ግብረ ሀይል ጽህፈት ቤት ተጠባባቂ ኃላፊ ፈትያ ሰይድ መንግስት የወንጀሉን አሳሳቢነት በመረዳት ተመላሽ ስደተኞችን ለማገዝ እና ወንጀሉን ለመከላከል እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በህገ ወጥ መንገድ ድንበርን የማሻገር ወንጀልን የተመለከተውን አዋጅ ለማሻሻል እየተሰራ እደሆነ የተናገሩት ተጠባባቂ ኃላፊዋ፤ ማሻሻያውም ዜጎች የሚያነሷቸውን ችግሮች እንዲፈታ ታሳቢ ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከ35 ሺህ በላይ ህጻናት፣ ወጣቶች እና ሴቶች በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ ሲሉ መያዘቸውን በቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ ተመላክቷል፡፡

በህገ ወጥ ዝውውሩ አማራ ክልል 32 በመቶ፣ ኦሮሚያ ክልል 31 በመቶ፣ ትግራይ ክልል ደግሞ 29 በመቶ የሚሆነውን ከፍተኛ ድርሻ እንደሚይዙም ነው የተገለጸው፡፡ ደቡብ አፍሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ ደግሞ ዜጎቹ በብዛት የሚሄዱባቸው ሀገሮች ናቸው፡፡ (ምንጭ፡-አብመድ)