በኬንያና በሳውዲአረቢያ መካከል የሚደረገው ድርድር ስኬታማ ከሆነ ኬንያ በቅርቡ 100 ሺህ ያህል ሰራተኞችን ወደ ሳውዲ እንደምትልክ ሲጂቲን ዘገበ፡፡
በሌላ በኩል ኳታር ገበያዋን ለኬንያ የስጋ ምርት ክፍት እንደምታደርግ አስታውቃለች፡፡
ይህ የታወቀው የሳውዲ አረቢያና የኳታር ባለስልጣናት ኬንያን በጎበኙበት ወቅት ባደረጉት ውጤታማ ውይይት መሆኑን ዘገባው አመላክቷል፡፡
የኳታሩ አሚር ሃማድ ቢን ካሊፋህ አል ታኒ በኬንያ የአንድ ቀን የስራ ጉብኘት ያደረጉ ሲሆን፤ የሳውዲ አረቢያ የንግድ ሚኒስትር መጅድ ቢን አብዱላህ አል ካሳቢ የተመራ 60 የግሉ ሴክተርና የመንግስት ባለስልጣናት የልዑካን ቡድንም በናይሮቢ ውይይት አድርጓል፡፡
የኬንያ መገናኛ ብዙሃን እንደገለፁት ፤ ተግባር ላይ የሚውል ከሆነ ሳውዲ አረቢያና ኬንያ ሁለቱንም ሃገሮች ሊጠቅም የሚችል በርከት ያሉ ስምምነቶች አድርገዋል፡፡
ከሳውዲ አረቢያ ጋር በተደረገው አዲስ ስምምነትም የመካከለኛ ምስራቅ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሿ ሳውዲ ከኬንያ የሰለጠኑ እና በከፊል ስልጠና የወሰዱ ነርስና ቴክኒሻኖችን የማስገባት ፍላጎት አላት፡፡
ሁለቱ መንግስታት በሳውዲ በአሰሪዎቻቸው በደል የሚደርስባቸውን የቤት ሰራተኞችን ጉዳይ ለመከታተልም ተስማምተዋል ፡፡
በርካታ ኬንያውያን የቤት ሰራተኞች በአሰሪዎቻቸው እንግልትና ድብደባ እንደሚደርስባቸውና ለሞትም እንደሚደርሱ በየጊዜው የሚወጡ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱ ዘገባው አስረድቷል፡፡
ኳታር በኬኒያ የናይሮቢን የፋይናንስ ማእከል ለመገንባትም ተስማምታለች ፤ ኬኒያ ከ2014 ጀምሮ በአፍሪካ ዋነኛ የፋይናንስ ማእከል ለመሆን እቅድ ይዛ የነበረ ቢሆንም በጉዳዩ የህግ ማዕቀፍ አለመኖሩ እንቅፋት መሆኑን ዘገባው አትቷል፡፡
የኳታሩ አሚርና ተወካዮቻቸው ከደቡብ ሱዳን ኢትዮጲያ የሚዘረጋውን የላሙ ወደብ የትራንስፓርት ኮሪደር ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልፀዋል ፡፡
ወደቡ ሲጠናቀቅ ለብዙ ኬኒያውያን የስራ እድል እንደሚፈጥር ዘገባው አመልክቷል-(ኢዜአ) ፡፡