ናሬንድራ ሙዲ የፊታችን ማክሰኞ ኡጋንዳን ይጎበኛሉ

የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሙዲ የፊታችን ማክሰኞ ኡጋንዳን ይጎበኛሉ፡፡

ያደጉ እና በማደግ ላይ ያሉት ሃገራት ከወትሮው በተለየ መልኩ ዓይናቸውን ወደ አፍሪካ አዙረዋል፡፡

በዚህም በቁጥር በርከት ያሉ መሪዎችና ልኡካናቸው ወደ አህጉሪቱ በማቅናት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት እየተስማሙ ይገኛል፡፡

የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ከመሪዎቹ መካከል ሲሆኑ በሶስት የአፍሪካ ሃገራት ላይ የአምስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡

ጉብኝት ከሚደረግባቸው ሃገራት መካከል ደግሞ ኡጋንዳ አንዷ ነች፡፡

የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኡጋንዳ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ በተለይም በሁለቱም ሃገራት ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ይመክራሉ፡፡

ዴይሊ ሞኒተር እንደዘገበው ኡጋንዳ ምርታቸው የተጠናቀቀ እና ውድ የሆኑ እቃዎችን በከፍተኛ መጠን ከህንድ ታስገባለች፡፡

ከመድሃኒት ምርቶች እስከ የተለያዩ የተሸከርካሪ ዓይነቶችም ከህንድ ወደ ኡጋንዳ የሚገቡ ናቸው፡፡

ዘገባው ባንክ ኦፍ ኡጋንዳን ጠቅሶ እንዳስነበበው በፈረንጆቹ 2017 ሃገሪቱ ከ559 ሚልየን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ የተለያየዩ ምርቶችን ከህንድ ገቢ አድርጋለች፡፡

በሁለቱም ሃገራት የምጣኔ ሃብት ግንኙነት ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበው ከአምስት ዓመታት በፊት የተደረገው የንግድ ልወውጥ ሲሆን ይህም ኡጋንዳ ከህንድ ያስገባችው ምርት በዋጋ ሲተመን 1,263 ቢልዮን ዶላር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ኡጋንዳ በበኩሏ በ2007 ወደ ህንድ ከላከቻቸው 3 ነጥብ 2 ሚልዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በ2017 በመላክ ገቢዋን ወደ 43 ነጥብ 7 ሚልዮን ዶላር ከፍ አድርጋለች፡፡

ይህም ሃገሪቱ ወደ ቻይና ልካ ከምታገኘው ገቢ በልጦ ተመዝግቧል፡፡

ሁለቱም ሃገራት አሁን ይደርሱበታል የተባለው ስምምነትም ከንግድ ባሻገር አጠቃላይ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውንም ያጠናክረዋል ተብሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኡጋንዳ በተጨማሪ ሩዋንዳንና ደቡብ አፍሪካን ይጎበኛሉ ተብሏል፡፡/ደይሊ ሞኒተር እና ዘ ኢኮኖሚክ ታይምስ/