ሩዋንዳና ህንድ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

ሩዋንዳ እና ህንድ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የበለጠ ማጠናከር የሚያስችላቸውን 7 ማእቀፎች ላይ ተስማሙ፡፡

ስምምነቶቹ የመከላከያ፤ የንግድ እና የባህል ልውውጦችን እንደሚያካትቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሩዋንዳ እና ህንድ ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ትብብር የበለጠ ለማተናከር ያስችላል የተባሉ 7 ጉዳዮች ላይ ከስምምነት መድረሳቸው ተነግሯል፡፡

የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ እና የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ  በሩዋንዳ ኡርግዊሮ መንደር ነው ስምምነቱን የተፈራረሙት፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ሞዲ ለሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት ሩዋንዳ ሲገቡ በፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች ያደረጉት ስምምነት በሀገራቱ ዘንድ ያለውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት እና ትብብር ወደ ላቀ ደረጅ ከፍ ለማድረግ እንደሚጠቅምም ነው የተመላከተው፡፡

ሀገራቱ የተፈራረሙአቸው ስምምነቶች እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ2018 እስከ 2022 የሚዘልቁ ሲሆን የመከላከያ፤ የንግድ እና የባህል ልውውጥ ትኩረታቸው ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት በግብርና፤በእንስሳት ሀብት ልማት፤በቆዳና ሌጦ ኢንዱስትሪዎች ላይም በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ካጋሜ ከስምምነቱ በኋላ በመሰብሰቢያ አዳራሽውስጥ ለነበሩ ጋዜጠኞች እንዳስታወቁት ማዕቀፎቹ ላይ የተደረሰው መግባባት ሀገራቱ ቅድሚያ ለሚሰጧቸው የልማት አቅጣጫዎች መሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ  እንደሚኖረው አንስተዋል፡፡

የሁለቱን ሀጋራ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናክር በማሰብ ህንድ በሩዋንዳ ኢምባሲዋን ለመክፈት ወስናለች፡፡ ሁለቱ አገራት እየሄዱበት ያለችውን ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖልካጋሜ አድናቆት ችረውታል፡፡

የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖልካጋሜ  የአፍሪካ ሀገራት በነጻ የንግድ ቀጠና ለማስተሳሰር የሚደረገው ጥረትን ህንድ ማዋዕለ ንዋይ በአፍሪካ እንድታፈስ የሚያበረታታ መሆኑን ለጠቅላይ ሚንስትር ሞዲ ተናግረዋል፡፡

ሞዲ በበኩላቸው ሀገራቸው ልምድ ባካበተችባቸው የቴክኖሎጂ፣  የመሰረተ ልማት ግንባታ እና የፋይናንስ አስተዳደር ዘርፎች ልምዷን ለሩዋንዳ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን ገልፀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም ሩዋንዳ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበችባቸው ነው ባሉት የግብርናና ገጠር ልማት ስራዎች ሩዋንዳ ከህንድ ልምድ መቅሰም እንዳላትም ጠቁመዋል፡፡

ይህ በሩዋንዳ የመጀመሪያ ነው የተባለለት የህንድ ጠቅላይ ሚንስትር ጉብኝት የመጣው የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ካጋሜ በቅርቡ ወደ ህንድ ማቅናታቸውን ተከትሎ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የሁለቱ ሀገራት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተጀመረተበት እኤአ  ከ1999 ጀምሮ የሁለቱ ሀገራ ትብብር በየአመቱ እድገት እያሳየ መምጣቱ ኦል አፍሪካን ዶት ኮም ይዞት የወጣው ዘገባ ያስረዳል፡፡