ሳዑዲ አረቢያ ለሱዳን 250 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አደረገች

ሱዳን ያጋጠማትን ምጣኔ ኃብታዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ለማስታገስ ይረዳታል በሚል ሳዑዲ አረቢያ 250 ሚሊየን ዶላር ገንዘብ በሱዳን ማዕከላዊ ባንክ ተቀማጭ እንዳደረገች አስታውቃለች።

የገንዘብ ስጦታው ከዚህ ቀደም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከለገሰችው ገንዘብ ጋር ተደምሮ አገሪቷ የገባችበትን የምጣኔ ኃብት ቀውስ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ያስታግስላታል ተብሏል።

ይህም የአገሬው ሰው ገንዘብ ለማውጣት በባንክ ደጅ የሚያደርገውን ሰልፍ ይቀንሳልም ተብሏል።

በሱዳን ከባንክ ወጪ ማድረግ የሚቻለው ከፍተኛው ገንዘብ 40 ዶላር (አንድ ሺህ አንድ መቶ ብር ገደማ) ሲሆን፤ ነዳጅ ለመሙላትም በሚያቃጥለው ሙቀት ለሰዓታት መሰለፍን ይጠይቃል።

በአውሮፓውያኑ 2011 ደቡብ ሱዳን የአገሪቱን አብዛኛውን የነዳጅ ሃብት ይዛ ከተገነጠለች ወዲህ ሱዳን ቀውስ ውስጥ ትገኛለችም ነው የተባለው።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር ይጠቀሙት የነበረውና ሥልጣናቸውን ለማራዘም ሲሉ ያወጡት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር አብዛኛውን በጀት ያውሉት የነበረው ለደህንነትና ለወታደራዊ ወጭዎች ሲሆን፣ ከቻይና፣ ኳታርና ሳዑዲ አረቢያ ጋር በፈጠሩት ጥብቅ ግንኙነትም የገንዘብ ድጋፍና ብድር ያገኙ ነበር፤ የተደረገላቸውን የገንዘብ ድጋፍ ለመክፈልም በየመን በሳዑዲ ለሚመራው ጦር በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ልከዋል።

በሱዳን ከፍተኛ ሆነ የሕዝብ ተቃውሞ የተቀሰቀሰው በአገሪቱ የምግብና የነዳጅ ዘይት ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ ሲሆን ባለፈው ወር ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣናቸው መውረዳቸው ይታወሳል።

ሱዳን በወታደራዊው የሽግግር መንግሥት እየተዳደረች ሲሆን፣ ተቃዋሚዎች ግን እስካሁን ድረስ አገሪቷ እየተመራች ያለችው በቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር ወታደር ሲሆን ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ጥብቅ ግንኙነትም አላቸው ብለዋል።

በመሆኑም አገሪቷን ለማረጋጋት አጠቃላይና ተገቢ የሆነ ለውጥ እንፈልጋለን በማለት ባለው የሽግግር መንግሥት ላይ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል።

አገሪቷን በዚህ የሽግግር ወቅት የሚመሩት ጄነራሎች ይህንን ሕልማቸውን ለማሳካት እንደቆሙ እየተናገሩ ነው። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)