ኬንያ በአንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር የሰራችውን የባቡር መንገድ ልትመርቅ ነው

ኬንያ የባቡር መንገዷ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን የኬንያ ባቡር መንገድ አስታውቋል።

አዲሱ የኬንያ የባቡር መስመር ከመዲናዋ ናይሮቢ ወደ ናይቫሻ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ተብሏል።

መስመሩ ለጊዜው አገልግሎት የሚሰጠው ለሰዎች ሲሆን የጭነት ማጓጓዝ አገልግሎት ደረቁ ወደብ እስኪገነባ ድረስ ይጠበቃል ነው የተባለው፡፡ ግንባታውም ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚወስድም ተገምቷል።

ለዚህም በአካባቢው የሚኖሩ የማሳይ ማህበረሰብ ግንባታውን በመቃወም ጉዳዩን ወደ ፍርድ በመውሰዳቸው እንደሆነ ተገልጿል።

በቻይና ኮሚዩኒኬሽንና ግንባታ ኩባንያ የተገነባው ይህ መስመር 120 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ሲሆን 1.4 ቢሊዮን ዶላር ፈጅቷል።

የተጓዦች አገልግሎት ከአስራ ሁለቱ ጣቢያዎች በአራቱ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀመር ዘ ቢስነስ ደይሊ ኒውስፔፐር የኬንያ የባቡር አገልግሎት ኃላፊ የሆኑት ፊሊፕ ማይንጋን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

የመጀመሪያው የባቡር መንገድ ከመዲናዋ ናይሮቢ ወደ ሞምባሳ ከሁለት አመት በፊት በተመረቀበት ወቅት ከፍተኛ ደስታና ፈንጠዝያ የነበረ ሲሆን ይህ መስመር ግን እንደ መጀመሪያው አልሆነም ተብሏል። በወቅቱም ኬንያ ለምርጫ ስትዘጋጅ ነበር።

የአዲሱ የባቡር መንገድ ዋጋ ከአለም አቀፉ ስታንዳርድ አንፃር ጋር ሲታይ ሶስት እጥፍ እንዲሁም መጀመሪያ ያወጣል ተብሎ ከተገመተው አራት እጥፍ ነው ተብሏል።

መንግሥት ዋጋው እንዲህ ለምን ናረ ለሚለው የሰጠው ምክንያት የመልክአ ምድሩ አስቸጋሪነት ድልድዮችንና ቱቦችን በመገንባት ላልታሰበ ወጪ እንደተዳረጉ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለመሬት ካሳ ተከፍሏል ተብሏል።

ከዚህ ወጪ ውስጥ 80% የተገኘው ከቻይና በተገኘ ብድር ነው።

የባቡር መስመሩ የመጀመሪያ እቅድ ከሞምባሳ- ኪሱሙን በመሻገር ኡጋንዳ ይደርሳል ተብሎ ነበር።

አገሪቷ ይህንን የባቡር መስመር ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ 3.3 ቢሊዮን ዶላር ብድር ያስፈልጋታል ተብሏል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)