የአፍሪካ ህብረት በኢሬቻ በዓል ላይ ሕይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያዊያን የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገለጸ

የአፍሪካ ህብረት በኢሬቻ በዓል ላይ በተፈጠረ መገፋፋትና መረጋገጥ ሕይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገለጸ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶክተር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ፥ በኢሬቻ በዓል ላይ በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እንዲሁም ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።

 የኢትዮጵያ መንግሥት የአደጋውን መንስዔዎች በማጣራትና ተጠያቂዎችን ለፍርድ ለማቅረብ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንዳለውም አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ጎን በመቆም ድጋፍ እንደሚያደርግም ሊቀመንበሯ አረጋግጠዋል።

ከህብረቱ በተጨማሪ የተለያዩ ተቋማት ሀዘናቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው።

የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ በበኩሉ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ተመኝቷል።

በተመሳሳይ የትራንስፖርት ሚኒስቴር በአደጋው ዜጎች ሕይወታቸው በማለፉ ጥልቅ ኀዘን እንደተሰማው ገልጿል።

ኢሬቻን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት የንጹሃን ሕይወት መጥፋቱ አሳዛኝ ነው ብሏል በመግለጫው።(ኢዜአ)