በናይጀሪያ በቦኮሃራም ታፍነው የነበሩ 21 የቺቦክ ልጃገረዶች ተለቀቁ

በናይጀሪያ ጂቦክ እ ኤ አ በ2014 በቦኮሃራም ታፍነው ከተወሰዱት ልጃገረዶች መካከል 21ዱ መለቀቃቸው የአገሪቱ መንግስት አስታወቀ ።

የፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ቃል አቀባይ ጋርባ ሸሁ እንደገለጹት፤ የመንግስት አስተዳደር አካላት እና የሽብር ቡድኑ ሚሊሻዎች ባደረጉት ድርድር ነው ልጃገረዶቹ የተለቀቁት ።

በድርድሩ የተለቀቁት ተማሪዎች በአሁኑ ወቅት በፀጥታ ሀይሎች ጥበቃ እየተደረገላቸው ይገኛል ብሏል ።

በወቅቱ በቺቦክ በቡድኑ ታፍነው ከተወሰዱት ሴቶች መካከል እስካሁን ማምለጧ የተረጋገጠው ልጃገረድ አንድ ብቻ መሆኗ ይነገራል።

50 የሚጠጉ ልጃገረዶችም ታፍነው በተወሰዱበት እለት ሳያመልጡ እንዳልቀሩ የሚታመን ሲሆን፤ 218ቱ ሴቶች ግን እስካሁን ያሉበት አይታወቅም።

በማህበራዊ ሚዲያዎችም “ሴቶቻችን መልሱ!” የሚል ዘመቻ እንዲከፈት ምክንያት ሆኗል።

ቦኮ ሀራም ባለፉት ሰባት አመታት በሰሜን ምስራቅ ናይጀሪያ አመፅ መቀስቀስ ከጀመረ ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አፍኖ መውሰዱን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል፡፡

ቦኮ ሀራም ከሁለት አመት በፊት በሰሜን ምስራቅ ናይጀሪያ ቺቦክ ከተማ በትምህርት ገበታ ላይ የነበሩ 270 ልጃገረዶችን አፍኖ መውሰዱ የሚታወስ ሲሆን ፤ ይህን ድርጊቱንም አለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲያወግዘው እንደነበር አይዘነጋም- (ኤፍ.ቢ.ሲ)።