የጋምቢያው ፕሬዝዳንት ያህያ ጃሜህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸውን አስታወቁ ፡፡
ፕሬዝዳንት ያህያ ጃሜህ ትናንት የሶስት ወር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁት በሀገሪቱ ድህረ ምርጫ ሁከትና ብጥብጥ ይቀሰቀሳል ብለው በመስጋታቸው ነው የተባለው ፡፡
የጋምቢያን ሰላምና ጸጥታ የሚያደፈርስ ማንኛውም ሁከትና ብጥብጥ እና የህግ የበላይነትን የሚጻረር ድርጊት በጊዜያዊ አዋጁ መደንገጉን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል፡፡
የጋምቢያ ፓርላማም የአፍሪካ ህብረትና የቀጠናው አገሮች በአገሪቱ የውስጥ ጉዳዮች በህገወጥ መንገድ እጃቸውን አስገብተዋል በሚል ማውገዙን ነው የተገለጸው ፡፡
የፕሬዝዳቱን ውሳኔ ተከትሎም የአገሪቱ የውጭ ጉዳይን ጨምሮ ቢያንስ ሶስት ሚንስትሮች በገዛ ፍቃዳቸው ከስልጣናቸው መነሳታቸውን ተመልክቷል ፡፡
በሀገሪቱ የሚከሰተውን ግጭት ፈርተው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሴኔጋልና ጊኒ ቢሳው መሰደዳቸውንም እንዲሁ ፡፡
በሀገሪቱ ባለፈው ታህሳስ ወር በተካሄደ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በተቀናቃኛቸው እጩ ተፎካካሪ አዳማ ባሮው ሲሸነፉ መጀመሪያ ላይ የምርጫውን ውጤት በመቀበል ስልጣናቸውን በሰላማዊ መንግድ ለማስረከብ ቃል መግባታቸው ይታወቃል ፡፡
የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ግን በምርጫው ውጤት ላይ ለውጥ የማያመጣ ጥቂት ስህተቶች ተፈጥረዋል ማለቱን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ የስልጣን ጊዜያቸው ቢጠናቀቅም መንበረ ስልጣናቸውን እንደማያስረክቡ ነው ያስታወቁት ፡፡
የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም የዳኞች እጥረት በችሎቱ በመኖሩ በምርጫው የተነሱ አቤቱታዎችን እስከ መጪው ግንቦት ድረስ እንደማይመለከት በመናገሩ ፕሬዝዳንቱም እስከዚያው ድረስ ከስልጣናቸውን እንደማይነሱ ገልጸዋል፡፡
የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ተከትሎም በሀገሪቱ ሁከትና ብጥብጥ እንዳይከሰት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ችግሩን በሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈታ ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል ነው የተባለው ፡፡
በዚህም ምክንያት የቀጠናው ሀገራትና የአፍሪካ ህብረት ለፕሬዝዳንት ጃሜህ ስልጣን እውቅና እንደማይሰጡት አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ የስልጣን ጊዜያቸው ሲጠናቀቅ በሰላማዊ መንገድ ከስልጣናቸው ካልተነሱ በሴኔጋል የሚመራ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ጥምር ጦር ወደ ጋምቢያ እንደሚዘምት የቀጠናው ሀገራት እያስጠነቀቁ ነው፡፡
እንዲያውም የናይጄሪያ የጦር መርከብ ፕሬዝዳንቱ ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር በጋና የባህር ወደብ አቅራቢያ ማስፈሯን ነው የተገለጸው ፡፡
የጋምቢያው ፕሬዝዳንት እ.ኤ.አ በ1994 በወታደራዊ መፈንቅ ለመንግስት የሀገሪቱ መሪ መሆናቸው ይታወሳል-(ኤ ኤፍ ፒ) ፡፡