ባለፈዉ ታሕሳስ ወር በተደረገዉ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉት አዳማ ባሮ ትናንት በጎረቤት ሴኔጋል መዲና ዳካር ዉስጥ በሚገኘዉ በጋሚቢያ ኤምባሲ ማምሻውን ቃለ-መሃላን ፈፀሙ።
በጋምቢያ የተቀሰቀሰዉ ፖለቲካዊ ቀዉስ እንደቀጠለ ነዉ።
የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሀብት ማኅበረሰብ «ECOWAS» ስልጣን የሙጥኝ ያሉትን ጃሜን በኃይል ለማንሳት ጦሩን ወደ ሀገሪቱ ድንበር ማስጠጋቱ ተዘግቧል።
የሀገሪቱ ጦር ሠራዊት አዛዥ በዚህ የፖለቲካ ዉዝግብ ዉስጥ እሳቸዉም ሆነ ሠራዊታቸዉ እንደማይገባ አስታዉቀዋል።
የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢሳቱ ኒጄ ሳዴን ጨምሮ የአካባቢ እና የትምህርት ሚኒስትሮችም ስልጣናቸዉን መልቀቃቸዉ ተዘግቧል።
የሃገሪቱ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ጃሜ በስልጣን እንደሚቆዩ እየዘገቡ ነዉ።
ከትናንት በስትያ የስልጣን ዘመናቸዉ ያበቃዉ በምርጫ ተሸናፊዉ ያህያ ጃሜ ስልጣን አላስረክብም እንዳሉ ነዉ።
የተመራጩ ፕሬዚዳንት አዳማ ባሮ ደጋፊዎች በበኩላቸዉ የተቃዉሞ ጥሪን ለማሰማት ዝግጅት ላይ ናቸዉ።
አንድ ስማቸዉ እንዳይገለጽ የፈለጉ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ እንደገለፁት « ከኅብረተሰቡ ጋር እየተነጋገርን ነዉ። ምናልባት ትንሽ ፍርሀት ተጭኖአቸዉ ቤታቸዉ የተቀመጡ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ፍርሀታቸዉን አሸንፈዉ መዉጣት ይኖርባቸዋል። ወጥተን ለሰጠነዉ ድምጽ መከበር መቆም ይኖርብናል። ወጥተን ለአብዮታችን ዘብ መቆም ይኖርብናል» የተመድ የጸጥታዉ ምክር ቤት የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሀብት ማኅበረሰብ «ECOWAS» በጋምቢያ የሰላም የስልጣን ሽግግር ጣልቃ መግባት ስለመቻሉ ድምፅ መስጠቱን ነው የተመለከተው ።
የቻይና መንግሥት በበኩሉ በጋምቢያ የስልጣን ርክክቡ ባለመፈፀሙ የተነሳዉን ቀዉስ በሰከነ መንገድ መፍትሄ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይገባል ሲል ጥሪዉን አስተላልፏል