በደቡብ ሱዳን ያለው ግጭት በተለይም ሴቶችን ለችግር እያጋለጣቸው በመሆኑ ጉዳዩ እደሚያሳስበው የአፍሪካ ሕብረት ገለጸ፡፡
ግጭቱ ወደ ኢትዮጵያና ኬንያ በርካታ ደቡብ ሱዳናውያን እንዲሰደዱ ምክንያት እንደሆነ ነው የተመለከተው፡፡
ሕብረቱ በተለይም ግጭት ባለባቸው የአፍሪካ አገሮች ያሉ ሴቶችን ሊያጋጥማቸው ከሚችሉ ችግሮች ለመታደግ የሚያስችል ቅስቀሳ ለ16 ቀናት እንደተደረገ የሕብረቱ የሴቶችና ልማት ዳይሬክተር ማዋካባ ዊለር ገልጸዋል፡፡
በደቡብ ሱዳን ያለውን የሴቶችን ተጨባጭ ሁኔታ ለመገንዘብ እንዲቻልም በሀገሪቱ ለሶስት ቀናት እንደቆዩና በቆይታቸውም ግጭቱ በሴቶች ላይ ያስከተለውን የጉዳት መጠን መገንዘብ እንደቻሉ ነው የጠቀሱት፡፡
ዳይሬክተሯ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የደቡብ ሱዳን ኃላፊዎች ጋር የሴቶችን ሕይወት ማሻሻል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደመከሩም ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት አራት ዓመታት የአፍሪካ ሴቶችን በትምህርት በማሳተፍ ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ለመሳደግ በተደረገው ጥረት ውጤት ቢመዘገብም ችግሮቹ ግን አሁንም ድረስ ዘልቀው እንደቀጠሉ ነው ያመለከቱት ፡፡
የሲቪል ማህበረሰቡም የሴቶችን ድምጽ እንዲሰማና ምላሽ እንዲሰጥም ዳይሬክተሯ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገሮች ላይ የሴቶችን ችግር ለመቅረፍና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤቶች እንተመዘገበ ታውቋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት በዚህ ረገድ እያበረከተው ያለው አስተዋፅኦ ሚና ከፍተኛ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡
ትርጉም -በሰለሞን ዓይንሸት