በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እንደሚሠሩ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ተናገሩ

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት የቀድሞ  የቻድ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር  ሙሳ ፋቂ  በሥልጣን  ዘመናቸው በአፍሪካ  ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን  እንደሚሠሩ ተናግረዋል ።   

ሙሳ ፋቂ ማህማት ልምድ ያላቸው የ56 ዓመት ፖለቲከኛ  ሲሆኑ  በተለያዩ  ፈታኝ  የሥራ ኃላፊነት ተመድበው ብቃታቸውን  ማሳየታቸው  ተገልጿል ።

ሙሳ ፋቂ  በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጊዚያዊ መቀመጫ የቻድ ተወካይ  እጩ መሆን የቻሉ  ሲሆን  ለአፍሪካ ህብረት  ኮሚሽነርነት መመረጥ ችለዋል ።  

የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ኮሚሽን  እኤአ በ2013  በናይሮቢ ከተማ በተካሄደው  ጉባኤ የመሪነት  ሚና የተጫወቱት ሙሳ ፋቂ  በአፍሪካ   ሽብርተኝነትን በመዋጋት  ረገድ ተገቢውን ሚና ተጫውተዋል ።  

ሙሳ ፋቂ  በአገራቸው በጠቅላይ ሚንስትርነትና በውጭ ጉዳይ ሚንስትርነት  ከማገልገላቸውም በላይ  ቻድ  ባካሄደችው የፀረ -ሽብር  ዘመቻ  ከሊቢያ ፣ ማሊ ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ማዕከላዊ የአፍሪካ ሪፐብሊክና ከሳህል አካባቢ አገራት ጋር የተቀናጀ  የዘመቻ  እንቅስቃሴ  ለማድረግ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ።   

በፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ  የሰላምና ፀጥታ ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ሌሲል ሎውን ቫድራን  በበኩላቸው ለዶቼዴሌ እንደገለጹት  ሙሳ በትውልድ አገራቸው  ሽብርን  ለመግታት  ወታደራዊ እርምጃ  እንዲወሰድ በማድረግ  የሚታወቁ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የቀድሞ  የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ዶክተር ድላሚኒ ዙማ ግጭት በሚባዛባት አፍሪካ በተለያዩ  አገራት ቀውሶች ሲከሰቱ ችላ በማለት እንደሚተቹ ቫደራን አስረድተዋል ።

በተለይ  አምስቱ የሳህል አገራት የሆኑት ሞሪታኒያ ፣ ማሊ ፣ኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶ እና ቻድ በፈጠሩት የፀረ-ሽብር ዘመቻ ጥምረት  ሙሳ ፋቂ የአገራቱ የውጭ ጉዳይ የሚንስትሮቹ ሊቀመንበር በመሆኑን  ከፍተኛ ኃላፊነታቸውን እንደተወጡ ቫድራን አብራርተዋል ።

የቻድ ወታደሮች  በሙሳ ፋቂ መመረጥ  የተሰማቸውን ደስታ  በቻድ ዋና ከተማ ኒጃሚና አቅራቢያ በሚገኝ ወታደራዊ ሠፈር  መግለጻቸውም  ተመልክቷል ።

በተጨማሪም  ሙሳ  የአፍሪካ  ህብረት ኮሚሽነርነት መመረጥ አውሮፓንም ሆነ አሜሪካን  የሚያስደስት ያስደስታል  ተብሎ  የሚጠበቅ ሲሆን  የተለያዩ  እስላማዊ አክራሪ  ቡድኖችና ቦኮሃራምን ለመዋጋት  ድጋፍ ሲያደርጉ  ቆይተዋል ።

የፈረንሳይ  የፀረ-ሽብር  ኦፕሬሽን  ዋና መቀመጫም  በቻድ መሆኑ  ይበልጥ  ከአፍሪካ ህብረት ጋር ያለውን  ግንኙነት ያጠናክረዋል ተብሎ ይጠበቃል ።     

የአፍሪካ  ህብረት  ከስድስት ወራት  በፊት ባካሄደው  የህብረቱ የኮሚሽነር ምርጫ   አንድም እጩ  ከ ሁለት ሦስተኛ  በላይ ድምጽ  ያለገኘ በመሆኑ   ምርጫው  በጥር ወር እንዲካሄድ  በተወሰነው መሠረት  ከትናንትና በስተያ  ሙሳ ፋቂ  ከኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሚና ሞሃመድ  የተሻለ ድምጽ  በማግኘት  ኮሚሽነር መሆን ችለዋል ።  

አዲሱ  ተመራጭ  የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር  ሙሳ ፋቂ  የህግ ትምህርታቸውን  በብራዛቪል እና ፓሪስ  የተከታታሉ ሲሆን  በሥልጣን  ዘመናቸው  በአፍሪካ  ከጠመንጃ ተኩስ ይልቅ   የአፍሪካውያን ባህላዊ ዝማሬዎችና የፋብሪካዎች ድምጽ እንዲሰሙ  በትኩረት እንደሚሠሩ  ተናግረዋል ።

በእሳቸው የአራት ዓመት ቆይታም   በአፍሪካ ልማትና የፀጥታ ጉዳይ  ቅድሚያ የሚሠጣቸው አጀንዳዎች እንደሚሆኑንና አስፈላጊም ከሆነ በአፍሪካ ህብረት ድርጅትም ለውጥ እንደሚያደርጉ  አስገንዝበዋል ።    ( ምንጭ ዶቼቬሌ )