የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተቃዋሚ ኃይሎች ግብጽ በደቡብ ሱዳን አማጺ ኃይሎች ይዞታ ላይ የቦንብ ድብደባ አካሂዳለች በሚል ክስ አቀረቡ።
አማጺ ኃይሎች ባወጡት መግለጫ እንዳመለከቱት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የደቡብ ሱዳን ቀውስን ወደ አካባቢያዊ ጦርነት እንዲያመራ እያደረጉ ይገኛሉ ።
ደቡብ ሱዳን አንደ አገር ከተመሠረተች በኋላ እኤአ በታህሳስ 15 2013 በአገሪቱ በተፈጠረው አዲስ ግጭት የሰላም ድርድር እየተካሄደ ሲሆን እኤአ በ2015 በሁለቱ ተቀናቃኞ ሳልቫኪርና ሪክ ማቻር መካከል አዲስ የሰላም ስምምነት የተደረሰ ቢሆንም እስካሁን ፍሬ ማፍራት አልቻለም ።
የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተቃዋሚዎች በአሁኑ ወቅት ግብጽ የደቡበ ሱዳንን የፖለቲካ ሁኔታ ለማባባስ ጥረት እያደረገች መሆኑን እየተናገሩ ሲሆን ልክ ሩሲያ በሶሪያ ለአላሳድ መንግሥትን ለመደገፍ እንደምታደርገው የቦንብ ድብደባ ሁሉ ግብጽም የደቡብ ሱዳን መንግሥትን ለመደገፍ በአማጺያን ላይ ድብደባ እያደረገች ነው ብለዋል ።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ አህመድ አቡ ዘይድ በበኩላቸው ግብጽ የአይር ጥቃት ፈጸመች የተባለውን ውድቅ በማድረግ “ ግብጽ በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አትገባም ” የሚል ምላሽ ሠጥተዋል ። ( ምንጭ : www.breitbart.com)