በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተነሳውን የፀረ -ስደተኞች ተቃውሞ ለመበተን ፖሊስ አስለቃሽ ጭስና ውሃ መርጨቱ ተመልክቷል ።
በዕለቱ በፕሪቶሪያ ከተማ የውጭ ዜጎችና የደቡብ አፍሪካ ተወላጆች ዱላዎችን ፣ ድንጋዮችንና የስለት መሣሪያዎችን በመያዝ በተፋጠጡበት ወቅት ፖሊስ በመሃል በመግባት የመከላከል ሥራ ከማከናወኑም በላይ የፖሊስ ሄሊኮፕተሮች በከተዋማ ሲያንዣብቡ ነበር ።
ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ከሰልፉ በፊት ህዝቡ እንዲረጋጋ ጥሪ አቅርበው ነበር ። በደቡብ አፍሪካ በውጭ አገር ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃትና ማስፈራራትም ፕሬዚደንት ዙማ አውግዘዋል ።
ብዙ የደቡብ አፍሪካ ተወላጆች የውጭ አገር ስደተኞች የደቡብ አፍሪካ ተወላጆችን የሥራ ዕድል ወስደዋል ብለው ያምናሉ ።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በፕሪቶቲያ አካባቢ በጆሃንሰበርግ ደቡብ አፍሪካውያን ተደራጅተው በሶማሊያውያን ፣ በፓኪስታናውያንና የናይጄሪያውያን ሱቆችን አጥቅተዋል ዘርፋም አካሄደዋል ።
ፕሬዚዳንት ዙማ በተጨማሪም በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች ህግ አክባሪና ለአገሪቱም ኢኮኖሚ ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ በመሆኑ ሊከነሩ ይገባል ብለዋል ።
“ ሁሉም የውጭ ዜጎች ህገ ወጥ የሰውና አዘዋዋሪዎችና ዕፅ ነጋዴዎች አይደሉም ። ይህን አይነት ወንጀል የሚሠሩትን ከንጹሃኑ መለየት ይገባል ” ብለዋል ፕሬዚደንቱ ።
የደቡብ አፍሪካ የአገር ውስጥ ሚኒስትር በበኩላቸው ድርጅቶች ዶክመንት የሌላቸውን ሠራተኞች መቅጠራቸውን እንመረምራለን ብለዋል ።
ከተቃውሞ ጀርባ የሚገኙት የማሜሎዲ ኮንሰርንድ ሬዚደንት ቡድን እንደገለጸው ስደተኞች የዜጎችን የሥራ ድርሻ እየወሰዱ መሆናቸውንና በሴተኛአዳሪናትና በዕፅ ንግድ ላይ ተሠማርተዋል ይላሉ ።
በደቡብ አፍሪካ እኤአ በ2008 የጸረ ስደተኞች ተቃውሞ የተነሳ ሲሆን ከ60 ሰዎች በላይ ህይወታቸውን አጥተዋል ።